የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ እና ቬይትናም አረንጓዴ ኢኮኖሚ የመገንባት ራዕይ ይዘው እየሠሩ ነው- ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)

By ዮሐንስ ደርበው

April 19, 2025

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና ቬይትናም አረንጓዴ ኢኮኖሚ የመገንባት ራዕይ ይዘው እየሠሩ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር ዴዔታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ገለጹ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቬይትናም ቆይታን አስመልክቶ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም፤ ቬይትናም ከ20 እና 30 ዓመት በፊት በጦርነት የተጎዳች ሀገር ብትሆንም አሁን ላይ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ መሰለፏን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የልማት ትልሟን ለማሳካት የረጅም፣ የመካከለኛ እና የአጭር ጊዜ ዕቅድ አውጥታ እየሠራች መሆኗን ጠቅሰው፤ ቬይትናምም በተመሳሳይ የልማት ዕቅዷን ለማሳካት ባደረገችው ትጋት ውጤታማ ሆናለች ብለዋል።

ሀገሪቱ በኢንዱስትሪና ግንባታ ዘርፎች ባሳየችው እመርታ የዓለም የምርት ማዕከል ሆናለች ማታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ለዚህ ውጤት መመዝገብ ዕቅድን በአግባቡ ለመፈጸም መንግሥት ያሳየው ቁርጠኝነትና የሕዝብ ድጋፍ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያም በአጭር ጊዜ ውስጥ ብልጽግናዋን ለማረጋገጥ እያደረገች ያለችው ጥረት ውጤታማ እንደሚሆን ከቬይትናም ልምድ የወሰደችበት ነው ብለዋል።

እንደ ሚኒስትር ዴዔታው ገለጻ፤ ኢትዮጵያ እና ቬይትናም አረንጓዴ ኢኮኖሚ የመገንባት ተመሳሳይ ራዕይ ይዘው እየሠሩ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ንጹህ፣ አረንጓዴ፣ ለኑሮ አመቺና ዘላቂ ከተማ ለመገንባት እያደረገች ያለችው ጥረት ከቬይትናም ጋር እንደሚያመሳስላትም ገልጸዋል።

በጉብኝቱ ስማርት ሲቲ ግንባታ ላይ ቬይትናም ያላትን ልምድ መቅሰም መቻሉንም አንስተዋል፡፡