Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የትንሣኤ በዓልን ስናከብር በኅብረት በመቆምና በመደጋገፍ ሊሆን ይገባል- ርዕሳነ መሥተዳድሮች

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የተለያዩ ክልሎች ርዕሳነ መሥተዳድሮች ለትንሣኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት፤ በዓሉ የደስታ፣ የፍቅርና የበረከት እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡

ዘላቂ ሠላምን እውን ለማድረግ፣ የዴሞክራሲና የልማት ግንባታውን ሂደት ፈጣን፣ ዘላቂና ቀጣይ እንዲሆን ከማስቻል አኳያ የቤተ እምነቶችና የምዕመናን ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ ተሳትፏቸው እንዲጠናከር ጠይቀዋል፡፡

የእምነት ነፃነትን በአግባቡ የማሥተዳደር ባህልን በማጎልበት፣ የጋራ እሴቶችን መሠረት ያደረገ ኅብረ-ብሔራዊነትን ለማጠናከር እና ጠንካራ ሀገር ለመገንባት በጋራ እንትጋ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በተመሳሳይ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከደበ በመልዕክታቸው በዓሉን ስናከብር፤ ፈተናዎችን በፅናት በመሻገር ለክልላዊና ሀገራዊ የሰላምና የልማት ትልሞቻችን በጋራ በመረባረብ የኢትዮጵያን የመንሠራራት ጉዞ ለማፅናት በመነሣት ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

በዓሉን ስናከብር ክርስቶስ ዓለምን የማዳን ታላቅ ገቢር በትህትና መፈፀሙን በማሰብ፤ በየተሰማራንበት መስክ ሀገራችንና ሕዝባችንን በፍጹም ትህትናና ቅንነት ለማገልገል በመነሳት መሆን እንዳለበት በመግለጽ አደራ ብለዋል፡፡

የመተሳሰብ፣ የመጠያየቅና የመደጋገፍ እሴቶችን በማንገብ፤ ያለንን ለሌለው በማካፈል፣ አቅመ ደካሞችንና ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን በመደገፍ እና ራስን ለበጎ ተግባራት በማዘጋጀት ማክበር ይጠበቅብናል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አሻድሊ ሀሰን፤ በዓሉ ከሐይማኖታዊ ክንዋኔው በተጨማሪ የመተሳሰብ፣ የመተዛዘን እና የመረዳዳት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህ የመደጋገፍ ተግባርም ከበዓሉ ዕለት ውጭም በይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀው፤ በዓሉ የሠላም፣ የደስታ፣ የጤናና የበረከት እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ የሐረሪ ክልላዊ መንግስት በዓሉን አስመልክቶ ባስተላለፈው መልዕክት፤ ህዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን ሲያከብር የተቸገሩ ወገኖችን በማብላትና በማጠጣት እንዲሁም የተለመደ የመተዛዘንና የመረዳዳት ባህሉን በመተግበር መሆን እንዳለበት ገልጿል።

በተያያዘም ህዝበ ክርስቲያኑን ጨምሮ መላው የክልሉ ነዋሪ ሰላምን፣ አብሮነትን፣ መተባበርንና ወንድማማችነትን እንዲያጎለብቱ ብሎም በክልሉ ለተጀመሩ ሁሉን አቀፍ የልማት ተግባራት ስኬት ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርቧል።

Exit mobile version