አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የትንሣኤ በዓል እየተከበረ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል መምህራን እንደሚሉት፤ ትንሣኤ ምዕመኑ መከባበርና አንዱ ለአንዱ መልካም ማድረግን የሚማርበት ዐውድም ነው፡፡
በቤተ ክርስቲያን አስተምኅሮ ክርስቲያኖች በዓለ ትንሣኤን የሚያከብሩበት ዐውድ እና የሚገልጹበት ሃይማኖታዊ መስተጋብሮች እጅግ ብዙ መሆናቸውን በማንሳት፤ ከእነዚህ መካከል ለአብት ትንሣኤ “የድልና የሰላም” በዓል መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡
ካህናት እና ምዕመናን እየተቀባበሉ በቤተ ክርስቲያን የሚታወጀው የድልና የሰላም አዋጅ፤ “ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡ በታላቅ ኀይልና ሥልጣን፡፡ ሰይጣንን አሰረው። አዳምን ነጻ አወጣው። ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነት ከዛሬ ጀምሮ ሰላምና ደስታ ሆነ” በማለት ክርስቲያኖች ሰላምን ያውጃሉ።
በዚሁ ወቅትም በግዞት፤ በጎዳና ወድቀው ያሉትን ያስባሉ። ያላቸውን ያካፍላሉ ሲሉም መምህራኑ ያብራራሉ፡፡
ትንሣኤ ሥርወ ቃሉ “ተንሥአ” ከሚለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን፤ ፊደላዊ እና መንፈሳዊ ትርጓሜዎች አሉት፡፡
ፊደላዊ ትርጉሙ “ተንሥአ” ተነሣ፣ መነሣት፣ መንቃት፣ አነሣሥ ማለት ነው፡፡
መንፈሳዊ ትርጉሙ ደግሞ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በአምስት የተለያዩ የትርጉም ዓይነቶች ተከፍሎ እደሚተረጎም መምህራኑ ያስረዳሉ፡፡
እነሱም፦ 1. “ትንሣኤ” ማለት ሕሊና ወይም ንቃወ ሕሊና፤ ተዘክሮተ እግዚአብሔር ማለት ነው።
2. “ትንሣኤ” ልቡና ሲሆን፤ የታደሰ ሕይወትን መኖር ወይንም በታደሰ ሕይወት መመላለስ ማለት ነው፡፡
3. “ትንሣኤ” የሙታን በሥጋ መነሣት ወይም “ትንሣኤ ዘለኃሣር” ነው። ነገር ግን ይህ የኃጢአን ትንሣኤ ዘለዓለማዊ ሞት ይከተለዋል።
4. “ትንሣኤ” ክርስቶስ በኃይልና በሥልጣን ሞትን ድል አድርጎ መነሣት ነው፡፡ “አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቶአል” (1.ቆሮ.15:20) እንዲል።
5. “ትንሣኤ” “ትንሣኤ ዘጉባኤ” ነው። ይህም የባሕርይ አምላክ የኢየሱስ ክርስቶስን “ትንሣኤ” መሠረት ያደረገ ሲሆን፤ ከዓለም ኅልፈት በኋላ ሰው ሁሉ እንደየሥራው ለክብርና ለውርደት፣ ለጽድቅና ለኩነኔ በአንድነት የሚነሣው የዘለዓለም ትንሣኤ ይሆናል፡፡
በሌላ መልኩ የትንሣኤ በዓልን በምሥጢርም በይዘትም የሚመሳሰለው፣ ጥላውና ምሳሌው የሆነው “ፋሲካ” የሚለው ሥያሜ መሆኑን መምህራኑ ያስገነዝባሉ፡፡
“ፋሲካ” ማለት በአረማይክ “ፓስኻ”፣ በዕብራይስጥ ቋንቋ “ፐሳኽ” በጽርእ (ግሪክኛ) “ፓስቃ” እንደሚባል እና ወደ ግእዝና አማርኛ ቋንቋ ሲመለስም፤ ፍሥሕ፣ ዕድወት (ማዕዶት)፣ በዓለ ናእት (የቂጣ በዓል)፣ እየተቸኮለ የሚበላ መሥዋዕት፣ መሻገር፣ መሸጋገር ማለት ነው ይላሉ፡፡
ፋሲካ፤ እስራኤል ዘሥጋ ከግብጽ የባርነት ቀንበር ወደ ነፃነት የተላለፉበት፣ ከከባድ ሀዘን ወደ ፍጹም ደስታ፣ የተሸጋገሩበት በዓል ነበር፡፡ በዚህ ኦሪታዊ ምሳሌ በዓል አሁን አማናዊው በዓለ ትንሣኤ እንደተተካበት ያስረዳሉ።
እንደ መምህራኑ ገለጻ፤ ፋሲካ በዘመነ ሐዲስ እስራኤል ዘነፍስ የሆኑት ክርስቲያኖች ትንሣኤውን የሚያከብሩበት ዕለት ሆኖ በክርስቶስ ትንሣኤ፤ ከኃጢአት ወደ ጽድቅ፤ ከኃሣር፣ ከውርደት ወደ ክብር፤ ከጠላት ሰይጣን አገዛዝ ወደ ዘለዓለማዊ ነፃነት፤ ከአደፈ፣ ከጐሰቆለ አሮጌ ሕይወት ወደ ሐዲስ ማንነት የተሻገሩበት ታላቅ መንፈሳዊ የነፃነት በዓል ነው፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን በሞቱ ድል ነስቶ፣ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ በሥልጣኑ የተነሣው ጥንተ ትንሣኤው መጋቢት 29 ቀን 34 ዓ.ም እንደሆነ ታሪከ ቤተ ክርስቲያን ያስረዳል ይላሉ፡፡
መልካም በዓል!!
በዮሐንስ ደርበው