አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በላይነህ ክንዴ ግሩፕ ፋውንዴሽን (ቢኬጂ) የትንሣኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ በተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል ለወገኖች ማዕድ አጋራ፡፡
በመርሐ-ግብሩ ላይ የተገኙት የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አዲሱ ሻንቆ(ዶ/ር)÷ ቢኬጂ ፋውንዴሽንና ባለቤቱ አቶ በላይነህ ክንዴ የምገባ ማዕከሉን ከመገንባት አንስቶ በየቀኑ 500 ወገኖችን እየመገበ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የምገባ ስራው ተቋርጦ እንደማያውቅ ጠቁመው÷በላይነህ ክንዴ እና ድርጅታቸው ለሚያደርገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የቢኬጂ ፋውንዴሽ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ በላይነህ ክንዴ በበኩላቸው÷ ድርጅቶቻችን ባሉበት ቦታ ሁሉ የአቅማችንን ድጋፍ እያደረግን እንገኛለን ብለዋል።
በተጨማሪም ትውልድን የሚያንጹ ተቋማትንና መኖሪያ ቤቶችን ገንብተን እያስረከብን እንገኛለን ያሉት አቶ በላይነህ÷ በመስጠታችን በረከትና የህሊና ደስታን እናገኛለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ቢኬጂ ፋውንዴሽን ዛሬ ካከናወነው ማዕድ የማጋራት መርሃ ግብር በተጨማሪ በቡሬ ከተማ ለሚገኙ 1 ሺህ 300 ለሚደርሱ ወገኖች የበዓል መዋያ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ይታወሳል።
በዮሐንስ በቀለ