አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የትንሣኤ በዓልን ከካዛንቺስ ኮሪደር ልማት ሰራተኞች፣ ኮንትራክተሮች እና አማካሪዎች ጋር የትንሳዔ በዓልን አክብረዋል።
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሰራተኞችን በማበረታት እንኳን ለትንሣኤ በዓል አደረሳችሁ፤ በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር፣ የደስታ እና የመተሳሰብ እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ ብለዋል።
የኮሪደር ልማት ሰራተኞች ቀን ከሌት በመትጋት ከተማዋ ውብ ገጽታ እንድትላበስ ስላደረጉ ምስጋና አቅርበው፤ በእናንተ ትጋት ካዛንቺስ የኮሪደር ልማት እየተጠናቀቀ ነው ብለዋል።
በዚህም የሥራ ባህልን የሚቀይር ውጤት እየተገኘ መሆኑን ገልጸው፤ አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ እና አዲስ ለማድረግ ቀን ከሌት ለምታደርጉት ትጋት አመሰግናለሁ ብለዋል።