የሀገር ውስጥ ዜና

የምንከተለው የብዝኃ-ዘርፍ ኢኮኖሚ ውጤታማ መሆኑን ከቬይትናም ጉብኝት ተረድቻለሁ- ወ/ሮ ሙፈሪሃት

By Yonas Getnet

April 21, 2025

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሥራና ክኅሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመራ ልዑክ በቬይትናም ያደረገውን ጉብኝት በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም፤ ቬይትናም በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የሪፎርም ሥራዎችን በማከናወኗ ከቀውስ አዙሪት በፍጥነት መውጣት የቻለችበትን ሁኔታ አንስተዋል፡፡

ተወዳዳሪ ኢኮኖሚን የመገንባት ተልዕኮ የተሰጠው የሰው ሀብት ልማት ሥራ መሠራቱን አንስተው፤ በዘርፉ ቁልፍ ለውጥ በማድረግ በትምህርት እና ስልጠና ዘርፍ የረዥም ጊዜ ፍኖተ-ካርታ ተቀርጾ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያም በዘርፉ በርካታ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን አስረድተው፤ ዘርፉን በይበልጥ ማሳደግ እንዲቻል የትምህርት እና የስልጠና ስምምነት ከቬይትናም ጋር መፈረሙን አስታውቀዋል፡፡

በሥራ ፈጠራ እና በጥቃቅን እና አነስተኛ ቢዝነሶች ላይ ትኩረት ተደርጎ መሠራቱን እንደተመለከቱ እና ከዚህም ከፍተኛ ልምድ መቅሰማቸውን ተናግረዋል፡፡

ቬይትናም የሰው ሀብት ልማት ሥራን ከትምህርት እና ስልጠና ጋር በማስተሳሰር ጊዜውን የዋጀ እና ገበያ መር ወደሆነ የሰው ሀብት ልማት ሥራ መቀየራቸውን ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ ውስጥም ተመሳሳይ አቅጣጫ መያዙን ተናግረዋል።

የቴክኒክ እና ሙያ ስልጠና ሥርዓቱን የአረንጓዴ ልማት አካል አድርገው መሥራታቸውን ጠቅሰው፤ በኢትዮጵያ የቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት ሥርዓተ-ትምህርቶች የአረንጓዴ ልማት ቅኝት እንዲኖራቸው ማድረግ ላይ ተጨማሪ ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተገንዝበናል ብለዋል፡፡

በዮናስ ጌትነት