የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮ-ፓኪስታን የወዳጅነት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ተካሄደ

By Yonas Getnet

April 21, 2025

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 13፣2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮ-ፓኪስታን የወዳጅነት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) በተገኙበት በሲያልኮት ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል፡፡

በመርሐ ግብሩ ከ1 ሺህ በላይ የሀገሪቱ ተማሪዎች እና የከፍተኛ ትምህርት ማሕበረሰብ አባላት መሳተፋቸውን የኤምባሲው መረጃ ያመላክታል፡፡

አምባሳደር ጀማል (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት÷ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በተገበረችው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለአየር ንብረት ለውጥ ትግል አርአያ መሆን እንደቻለች ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በፓኪስታን በአየር ንብረት ለውጥ ትግል ያካበተችውን ልምድ ለማስተዋወቅ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር ስትሰራ መቆየቷን አንስተዋል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ባለፉት ስድስት ዓመታት ከ40 ቢሊየን በላይ ችግኞች መተከላቸውን አስገንዝበዋል፡፡

ይህም የደን መልሶ ማልማት እና ማስፋፋትን ከማሳደጉ በተጨማሪ በግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ የሥራ ዕድል ፈጥሯል ነው ያሉት፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በሁለቱ ወዳጅ ሀገራት መካከል የአየር ንብረት ጥበቃ ጥረቶችን በማጎልበት የትብብር መድረኩን እንደሚያሠፋ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።