የሀገር ውስጥ ዜና

በተደራጀ መረጃ ዓለም አቀፋዊ ተደራሽነትን ማስፋት ያስፈልጋል – አቶ አድማሱ ዳምጠው

By Melaku Gedif

April 21, 2025

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በተደራጀ መረጃ ዓለም አቀፋዊ ተደራሽነትን ማስፋትይገባል ሲሉ የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው ገለጹ፡፡

አቶ አድማሱ በቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ዓለም አቀፍ ዲፓርትመንት አዘጋጅነት ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ የሚዲያ መሪዎች የውይይት መድረክ ላይ ተሳትፈዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚው በዚህ ወቅት÷ፈጣንና ዓላማ ተኮር መረጃ አመለካከቶችን በሚቀርጽበት እና ተጽዕኖ በሚያሳድርበት ዘመን ሚዲያዎች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል።

በዚህም ሚዲያው ትክክለኛ መረጃን ተደራሽ በማድረግ በማህበረሰብ ግንባታ እንደ ድልድይ ሆኖ በማገልገል፣ ትክክለኛ ዘገባ በማቅረብ፣ የባሕል ልውውጥን በማስተዋወቅና ዓለም አቀፋዊ ውይይትን በማበልጸግ ሥራዎችን መስራት እንዳለበት ተናግረዋል።

በመገናኛ ብዙኃን አመለካከቶችን ለመቅረጽ፣ ለውጥን ለማነሳሳት እና በተለያዩ ማሕበረሰቦች መካከል ጥልቅ ግንዛቤን ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡

በሴሚናሩ የሚደረጉ የመረጃ ውይይቶች ምርጥ የሀገራት ተሞክሮዎችን የሚዳስሱ ሲሆን በትክክለኛ መረጃ ፍሰት ላይ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በብቃት በመጋፈጥ እና የዘመናዊ ሚዲያ ግንባታ ውስብስብ ችግሮችን ለመፍታትም መሰል መድረኮች ጠቀሜታቸው የጎላ ነው ብለዋል።

እንደ ሚዲያ በሀገር ገጽታ ግንባታ ሒደት ሃሳቦችን በመለዋወጥና እርስ በርስ በመማማር፣ ታማኝነት እና ግልጸኝነት ያለውን መረጃ ለአድማጭ ተመልካች እና ተከታይ ማድረስ አስፈላጊ ነው ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ኢትዮጵያና ቻይና ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ እና ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት በመሆናቸው በባህል፣ ንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ መሠረተ ልማት፣ ትምህርት እና ቴክኖሎጂን ጨምሮ ቁልፍ ዘርፎችን ለሚያጠናክሩ የሚዲያ ስራዎች ልዩ ትኩረት ይሰጣል ነው ያሉት፡፡

በተጨማም በመረጃ የተደገፈና በገጽታ ግንባታ ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፋዊ ትስስርን በማጠናከር ረገድ ያለንን ሚና ለማሳደግ እንሰራለን ብለዋል።