አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ለውጭ ባለሃብቶች ዝግ የነበሩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች መከፈታቸው በርካታ የውጭ ኩብንያዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ማስቻሉን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) እንደገለጹት÷ኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት ዓመታት በበርካታ የለውጥ ሒደት እያለፈች አመርቂ ውጤቶችን ማስመዝገብ ችላለች፡፡
ባለፉት የለውጥ ዓመታት ለውጭ ባለሃብቶች ዝግ የነበሩ ዘርፎች መከፈታቸውን ጠቁመው፥ በኢኮኖሚ ሪፎርሙ ኢንቨስትመንትን ሊደግፉ የሚችሉ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
የኢንቨስትመንት ህግን በማሻሻል ረገድ የተወሰዱ ርምጃዎች ከዚህ ቀደም ለውጭ ባለሃብቶች ተገድበው የቆዩ ዘርፎችን የከፈተ መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ቦርድ የውጭ ኩባንያዎች በጅምላ፣ ችርቻሮ እንዲሁም በወጪ እና ገቢ ንግዶች ላይ እንዲሰማሩ መፍቀዱን ጠቅሰዋል።
መንግስት ለረጅም ዓመታት ለውጭ ኩባንያዎች ዝግ ሆነው የቆዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎችን ክፍት ማድረጉ ለአብነትም እንደ ኢትዮ ቴሌኮምና የልዩ ኢኮኖሚ ዞን አዋጅ ኢንቨስትመንቱን የሚደግፉና የውጭ ባለሃብቶች በብዛት መጥተው እንዲሳተፉ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ባለፉት 9 ወራት ከፍተኛ አፈጻጸም ማስመዝገቡን የገለጹት ኮሚሽነሩ፥ ለአብነትም በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከአምናው የ2 ነጥብ 4 በመቶ ዕድገት መታየቱን ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡
ከሪፎርሙ አንጻር ኢትዮጵያ ካላት እምቅ አቅም አንጻር ከዚህም በላይ መጓዝ እንደሚገባ ጠቁመው፥ የጅምላና ችርቻሮ ወጪና ገቢ ንግድ መከፈቱን ተከትሎ ለ40 የውጭ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡
36 የሚሆኑት ደግሞ በሒደት ላይ መሆናቸውን ነው ኮሚሽነሩ ያስገነዘቡት፡፡
የድሬዳዋ ነጻ ንግድ ቀጣና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቆ ስራ ከጀመረ ወዲህ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ባለሃብቶችን ወደ ቀጣናው እንዲገቡ እያደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
በዚህም 11 የሚሆኑ ባለሃብቶች የገቡ ሲሆን÷ አንዳንዶች ሸቀጦችን ጭምር እያመጡ መሆኑን ጠቁመዋል።