ዓለምአቀፋዊ ዜና

የተለያዩ ሀገራት መሪዎችና የዓለም አቀፍ ተቋማት ሃላፊዎች በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ሕልፈት የተሰማቸውን ሃዘን ገለጹ

By Melaku Gedif

April 21, 2025

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የተለያዩ ሀገራት መሪዎች እና የዓለም አቀፍ ተቋማት ሃላፊዎች በሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ሕልፈት የተሰማቸውን ሃዘን ገልጸዋል፡፡

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ሕልፈት ጥልቅ ሃዘን እንደተሰማቸው በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት የሃዘን መግለጫ መልዕክት አስፍረዋል፡፡

በተመሳሳይ የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ፣ የአየርላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊዮ ቨራድከር፣ የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ እና የሌሎች ሀገራት መሪዎች በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ሕልፈት የተሰማቸውን ሃዘን ገልጸዋል።

እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ሕልፈት የተሰማቸውን ሃዘን ገልጸዋል።

በሀዘን መግለጫ መልዕክታቸውም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ለሰላም፣ ለፍትሕ፣ ለመልካምነት እና ለመንፈሳዊ መሪነት በጽኑ ሲተጉ የነበሩ መሆናቸውን አውስተዋል፡፡

የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷የካቶሊክ እና የዓለም ክርስቲያን ማህበረሰብ ትልቅ የሃይማኖት አባት አጥተዋል ሲሉ ባስተላለፉት የሃዘን መግለጫ መልዕክት ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ኡርሱላ ቮንዴር ሌይን በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ሕልፈተ ሕይወት የተሰማቸውን ሃዘን መግለጻቸው ተመላክቷል፡፡