Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በጅቡቲ ሕጋዊ የመኖሪያ ሰነድ የሌላቸው የውጭ ሀገር ዜጎች የመመለሻ ጊዜ አልተራዘመም – ኤምባሲው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በጅቡቲ ሕጋዊ የመኖሪያ ሰነድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን እና የሌሎች ሀገራት ዜጎች ወደየሀገራቸው የመመለሻ ጊዜ አለመራዘሙን በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታውቋል፡፡

ኤምባሲው÷የጅቡቲ መንግስት ሕጋዊ የመኖሪያ ሰነድ ሳይኖራቸው በሀገሪቱ ውስጥ የሚኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎች ከፈረንጆቹ ሚያዝያ 3 እስከ ግንቦት 2 ቀን 2025 ባለው ጊዜ ውስጥ በፈቃደኝነት ወደየሀገራቸው እንዲመለሱ ማሳወቁን አስታውሷል፡፡

ይህንን የማይተገብሩትን ደግሞ በፖሊስ ሃይል ወደመጡበት ሀገር እንዲመለሱ እንደሚደረግ ነው የተመላከተው፡፡

ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ኤምባሲው ከጅቡቲ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ሃላፊዎች ጋር የመከረ ሲሆን ÷ በዚህም በጅቡቲ የሚኖሩና ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ዜጎች ብዛት ስላላቸው እንዲሁም ትምህርት በመከታተል ላይ ያሉ ዜጎች ልጆቻቸው ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ መደረግ እንዳለበት መነሳቱን ጠቅሷል፡፡

በተጨማሪም ነጋዴዎች እቃቸውን አጣርተው መሸጥ ስላለባቸው እና በተለያዩ ስራዎች ተቀጥረው ለሚሰሩ ዜጎቻችን ያልተከፈሉ ውዝፍ ክፍያዎች ካሉ እንዲከፈላቸው እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በማንሳት ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው የመመለሻው ቀን ቢያንስ በ3 ወራት እንዲራዘም ጥያቄ አቅርቧል።

የጅቡቲ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አመራሮች በበኩላቸው÷ በሀገሪቱ ውስጥ የሚኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎች ከላይ በተጠቀሰው ጊዜ ለማስወጣት የተያዘው ዕቅድ የሚሻሻልበትና በልዩ ሁኔታ የሚታይ ጉዳይ እንደሌለ አስታውቀዋል፡፡

ይሁን እንጂ በኢትዮጵያውያን ባለቤትነት የተያዙ የንግድ ድርጅቶች (መደብሮች፣ ሱቅ፣ ወዘተ) ያላቸው ካሉም ሕጋዊ ባልሆነ ሁኔታ የተያዙበት መንገድ የሚመረመር መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ባለቤቶቹ በጅቡቲ መኖር የሚያስችላቸው ሕጋዊነታቸውን እስኪያረጋግጡ ድረስ ንብረታቸውን በአደራ ሰጥተው ሊሄዱ እንደሚችሉ አመልክቷል፡፡

በአሰሪዎች በኩል ለሰራተኞች ሳይከፈል የተጠራቀሙ ክፍያዎችን ከወዲሁ ከፍለው እንዲያጠናቅቁ ሚኒስቴሩ አሳስቧል፡፡

በፍርድ ቤት የተያዙ የዜጎቻችን ጉዳዮች በሚሲዮኑ በኩል በሚቀርቡ ማስረጃዎች ላይ በመመስረት በፍጥነት ታይተው መፍትሔ እንዲያገኙ እንደሚደረግ ነው የተገለጸው፡፡

ከጅቡቲ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር የዛሬ ዓመት የተሠጠን መግለጫ እንደ አዲስ በማስመሰል የሚሰራጨው መረጃ ሀሰተኛ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥቷል፡፡

በፍርድቤት የተያዘ የክፍያ ጉዳይ ያላቸው ዜጎች ጉዳያቸውን የሚያሣይ ማስረጃ በማቅረብ ኤምባሲ በመምጣት መመዝገብ እንደሚችሉ ተመላክቷል፡፡

ዜጎች ወደ ሀገር ቤት ከመመለስ ጋር ተያይዞ ዝርዝር መረጃዎች ከኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሚሰጥ አቅጣጫ መሰረት ኤምባሲው እንደሚያሳውቅ ጠቁሟል፡፡

Exit mobile version