አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሐረሪ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ በተገኙበት የክልሉ የበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት የሥራ አፈፃፀም ግምገማ እየተካሄደ ነው፡፡
አቶ ኦርዲን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ግምገማው በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና በመልካም አሥተዳደር ዘርፎች በዕቅድ የተያዙ ቁልፍ ሥራዎችን አፈፃፀም ጠንካራና ደካማ ጎኖች በመለየት ቀሪ ሥራዎችን በቀጣይ ተግባራዊ ለማድረግ ያግዛል፡፡
የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ እንዳመላከተው፤ የግምገማ መድረኩ ዛሬን ጨምሮ ለተከታታይ ሁለት ቀናት ይቆያል፡፡
የክልሉ የፕላን ኮሚሽነር ኢብሳ ኢብራሂም የካፒታል ፕሮጀክቶች አፈፃፀምን አስመልክቶ ባቀረቡት ሪፖርት፤ በዘጠኙ ወራት የገጠርና የከተማውን ማህበረሰብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ያቃለሉ 33 ፕሮጀክቶች ተጠናቀዋል ብለዋል።
ለሕብረተሰቡ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ የተቋማት ዕድሳትና ግንባታ እንዲሁም የዲጂታል ቴክኖሎጂ መሠረተ ልማቶች ዝርጋታ መከናወኑን ጠቁመዋል።