አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በ34ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር አርሰናል በሜዳው ኤሚሬትስ ምሽት 4 ሰዓት ላይ ክሪስታል ፓላስን ያስተናግዳል።
በ66 ነጥብ 2ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አርሰናል ከተከታዮቹ ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማስጠበቅ ከጨዋታው ሙሉ ሶስት ነጥብ ለማግኘት ይፋለማል።
በኦሊቨር ግላስነር የሚመራው ክሪስታል ፓላስ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ በ44 ነጥብ 12ኛ ላይ ይገኛል።
ሁለቱ ቡድኖች በሁሉም ውድድር ባደረጓቸው ያለፉት አምስት የእርስ በርስ ጨዋታዎች አርሰናል አምስቱንም በማሸነፍ የበላይ ነው።
አርሰናል ዛሬ ምሽት በክሪስታል ፓላስ ከተሸነፈ ሊቨርፑል የ34ኛ ሳምንት ጨዋታውን ሳያደርግ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ማንሳቱን ያረጋግጣል።
ትናንት ምሽት በተደረገ የ34ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ማንቼስተር ሲቲ አስቶንቪላን 2 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፏል።
የማንቼስተር ሲቲን የማሸነፊያ ግቦች ሲልቫና ኑኔስ ከመረብ ሲያሳርፉ÷የአስቶንቪላን ብቸኛ ግብ ደግሞ ማርከስ ራሽፎርድ በፍጽም ቅጣት ምት አስቆጥሯል።
ውጤቱን ተከትሎ ማንቼስተር ሲቲ በ61 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ አስቶንቪላ በ57 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በወንድማገኝ ጸጋ