አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኮይሻ የውኃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የግንባታ ሥራ የተራቆቱ ቦታዎችን ቀድሞ ወደነበሩበት ተፈጥሯዊ ይዞታ የመመለስ ሥራ እየተከናወነ መሆኑ ተገለፀ፡፡
በፕሮጀክቱ የአካባቢያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ዕቅድ ሥራ አስኪያጅ ግዛቸው ደሳለኝ እንደገለፁት፤ ለፕሮጀክቱ የግንባታ ሥራ ግብዓት የተቆፈሩ እና ተረፈ ምርቶች ተጠራቅመውባቸው የነበሩ ቦታዎችን ወደ ተፈጥሯዊ ይዞታቸው የመመለስ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡
በዚህም ፕሮጀክቱ ራሱን የቻለ የሥራ ቡድን እና የችግኝ ጣቢያ አቋቁሞ ከግንባታ ሥራው ጎን ለጎን የመልሶ ማልማት ሥራ እያከናወነ ነው ማለታቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መረጃ አመላክቷል፡፡
የተለያዩ ማሽነሪዎችና ወርክ ሾፖች የተተከሉበት ቦታን ጨምሮ በፕሮጀክቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ሌሎች ቀሪ ቦታዎችን ወደ ነበሩበት የመመለሱ ሥራ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡
የመልሶ ማልማት ሥራው የአካባቢውን ሥነ-ምኅዳር ለመጠበቅ ብሎም በቀጣይ የሚኖረው ሰው ሠራሽ ኃይቅ በደለል እንዳይሞላ በማድረግ ግድቡ የሚጠበቅበትን አገልግሎት እንዲሰጥ ያስችላል ብለዋል፡፡