ለኢንተርፕራይዞች ከ10 ቢሊየን ብር በላይ የሥራ ማስኬጃ ብድርና የማምረቻ ማሳሪያ ተሰራጨ

By Mikias Ayele

April 23, 2025

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለአምራች ኢንተርፕራይዞች ከ10 ቢሊየን ብር በላይ የሥራ ማስኬጃ ብድር እና የማምረቻ መሳሪያ መሰጠቱን የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት አስታውቋል፡፡

የተቋሙ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሮቤል አሕመድ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷የነባር አምራች ኢንተርፕራይዞችን  አቅም ለማጠናከርና አዳዲሶችን ለማቋቋም በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራት 2 ሺህ 752 አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች የተቋቋሙ ሲሆን ÷ 10 ሺህ 979 ነባር አምራች ኢንተርፕራይዞችን ደግሞ ማጠናከር መቻሉን ገልጸዋል፡፡

አዲስ አምራች ኢንተርፕራይዞችን በማቋቋምና ነባሮቹን በማጠናከርም ለ151 ሺህ 726 ዜጎች የሥራ እድል መፈጠሩን ነው የተናገሩት፡፡

ለኢንተርፕራይዞች የመስሪያ ቦታ እና የብድር አቅርቦት ተደራሽ ከማደረግ አንጻር በትኩረት እና በትብብር መሰራቱን አመልክተዋል፡፡

በዚህም ለ1 ሺህ 209 አምራች ኢንተርፕራይዞች 6 ቢሊየን 63 ሚሊየን 775 ሺህ ብር በላይ  የሥራ ማስኬጃ ብድር መሰራጨቱን ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም ለ889 አምራች ኢንተርፕራይዞች 4 ነጥብ 32 ቢሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የማምረቻ መሳሪያዎችን ማሰራጨት ተችሏል ነው ያሉት፡፡

በመላኩ ገድፍ