Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በላሊበላ መካነ-ቅርስ እድሳት ፕሮጀክት ሂደት ላይ ያተኮረ ምክክር ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቱሪዝም ሚንስትር ሰላማዊት ካሳ ከፈረንሳይ አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክ እና ከላሊበላ መካነ-ቅርስ ጥገና ክትትል ኮሚቴ ጋር ተወያይተዋል፡፡

ውይይቱ በፈረንሳይ መንግስት ድጋፍ በሚከናወነው የላሊበላ መካነ-ቅርስ የእድሳት ፕሮጀክት ሂደት ላይ ያተኮረ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

የጥገና ሥራ ጥናትን በተመለከተ የወጣው ዓለም አቀፍ የጨረታ ሂደትና አጠቃላይ የጥገና ሥራውን አስመልክቶም በሚደረገው ሳይንሳዊ ጥናት ዙሪያ ዝርዝር ምክክር ተደርጓል::

የፈረንሳይ መንግሥት በቱሪዝም ዘርፍ እያደረገ ላለው ድጋፍ ያመሠገኑት ሚኒስትሯ፤ የላሊበላ መካነ-ቅርስ እንክብካቤ፣ የታላቁ ቤተመንግሥት እድሳት እንዲሁም ብሔራዊ ሙዚዬምን ለማዘመን የተጀመረውን ሥራ በመደገፍ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን፣ የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን እና የላሊበላ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች የተካተቱበት አማካሪ ኮሚቴ መቋቋሙንም ሚንስትሯ አስታውቀዋል፡፡

በውይይቱ የስልጠና መድረክ እንዲመቻችም አቅጣጫ ተቀምጧል።

አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክ በበኩላቸው፤ የላሊበላ ቅርስ እንክብካቤ የሚመለከቱ ሥራዎች በተለይም የታቀደው ጥናት በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ጥረት እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል፡፡

በውይይቱ የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስና የቅዱስ ላሊበላ ደብር የበላይ ጠባቂ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስን ጨምሮ የላሊበላ ከተማ ከንቲባ እንዲሁም የቱሪዝም ሚኒስቴር ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

Exit mobile version