Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ጠንካራ ተቋም በመገንባት የሴቶችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባል – ወ/ሮ ሎሚ በዶ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠንካራ ተቋም በመገንባት የሴቶችን ተሳትፎና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ም/አፈ ጉባዔ እና የሴቶች ኮከስ የበላይ ጠባቂ ወ/ሮ ሎሚ በዶ ገለጹ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴት ተመራጮች ኮከስ የሥራ አስፈጻሚ አባላት የኮከሱን የሦስት ዓመት ተኩል የተግባር አፈጻጸም ገምግመዋል፡፡

ወ/ሮ ሎሚ በዚህ ወቅት÷ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሠሩ ሥራዎች ሁሉ የሴቶችን ተሣታፊነትና ተጠቃሚነት ታሳቢ ሊያደርጉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ለአብነትም በሀገራዊ ምክክር ሒደቱ፣ በቀጣይ በሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫና በሌሎች ሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ፍትሃዊ ውክልና እንዲኖራቸው ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

በዚህም መሰረትም የሴቶችን ተሳትፎ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለማሳደግ ከወዲሁ በቅንጅት መስራት ይገባል ነው ያሉት፡፡

ኮከሱ የሥርዓተ ጾታ እኩልነትን የሚያረጋገጡ ተግባራትን በየተቋማቱ መፈጸማቸውን የማረጋገጥ ሥራ በተጠናከረ መልኩ እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ ጾታዊ ጥቃትን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ኮከሱ የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡

በተለይም ሴት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ከወዲሁ ለማብቃት በትኩረት እንደሚሰራ መጥቀሳቸውን የም/ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version