Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢትዮ ቴሌኮምና ቪዛ የዲጂታል ፋይናንስ ተደራሽነትን ለማጠናከር መከሩ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ከቪዛ ኢንክ የደቡብና ምስራቅ አፍሪካ ሪጅን ም/ፕሬዚዳንት ሚካኤል በርነር ጋር ተወያይተዋል፡

በውይይታቸውም በዓለም አቀፍ የዲጂታል የፋይናንስ አገልግሎቶች ላይ አዳዲስ የትብብር ዕድሎችን መፈተሽ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል፡፡

በዚህም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የዋሌት ቨርቹዋል ቪዛ ካርድና በቪዛ ዳይሬክት እንዲሁም በቴሌብር ረሚት በኩል የሚሰጡ ዓለም አቀፍ ሐዋላ አገልግሎቶች የሚገኙበት ደረጃ ቀርቧል።

በሐዋላ አገልግሎቶቹ የተመዘገበው አበረታች አፈጻጸምና በተለይም ሀገራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ እያደገ በመጣው የገበያ ዕድል ዙሪያም ገለጻ ተደርጓል፡፡

እንዲሁም የደንበኞችን ፍላጎት መሰረት በማድረግ በዓለም አቀፍ ሐዋላ አገልግሎቶች ላይ ቀጣይነት ያለው ማሻሻያ እየተከናወነ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ÷ ቴሌብር ለአካታች እና ተደራሽ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ቁልፍ ሚና በመጫወት ላይ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ቴሌብር ከቪዛ ዓለም አቀፍ ኔትወርክ ጋር በመጣመር አዳዲስ ፈጠራ የታከለባቸው የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶች ማቅረብ የሚቻልበት ዕድል መኖሩን አንስተዋል።

የፋይናንስ ተደራሽነትን የሚያሰፉና በኢትዮጵያ የዲጂታል ፋይናንስ ባሕል ግንባታ ላይ ጉልህ አሻራ ለማኖር ተቀራርቦ የሚሰራ የጋራ ቡድን ለማቋቋም መስማማታቸውንም የኢትዮ ቴሌኮም መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version