አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ዘርፉ ለሀገሪቱ ትላልቅ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም የላቀ አስተዋፅኦ አበርክቷል ሲሉ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ።
ሚኒስቴሩ እና ተጠሪ ተቋማት በ2017 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ተስፋ ሰጭና አበረታች ስኬቶች ማስመዝገባቸው ተገምግሟል።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን የኤርፖርት መሠረተ ልማት የመገንባት እና የሀገሪቱን የኤርፖርቶች መዳረሻ የመጨመር፣ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ተደራሽነትን የማስፋፋት ሥራ መሰራቱ ተገልጿል።
እንዲሁም የኤር ናቪጌሽን መሠረተ ልማት በመገንባት፣ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው እድገት የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ የማሳደግ፣ የአየር ትራንስፖርት አደጋ ሥጋትን መቀነስ እና ደህንነት የማረጋገጥ ተግባር መከናወኑ ተነግሯል።
የመንገድ ደህንነት ህጎችን ተግባራዊ የማድረግ እና የመቆጣጠር፣ የመንገድ ደህንነት ኢንስፔክሽን እንዲሁም አደጋ የሚበዛባቸው ቦታዎች በመለየት ማሻሻያ እንዲደረግባቸው የማድረግ ሥራዎች መሰራታቸው ተጠቅሷል።
የሀገሪቱን የገቢና ወጪ ዕቃዎች የማቀላጠፍ፣ ለአዲስ የመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ኦፕሬተር ፈቃድ የመስጠት እንዲሁም የሎጂስቲክስ ወጪን መቀነስ ሥራዎች መከናወናቸው ተገምግሟል።
የሀገሪቱን ገቢና ወጪ ጭነት የማጓጓዝ፤ የመንገደኞት ትራንስፖርት አገልግሎትን የመጨመር፣ የባቡር መሰረተ-ልማት ጥገና በማድረግ ተደራሽነትን የማሻሻል፣ የባቡር ደህንነትና የመድረሻ ሰዓት ማሻሻል ሥራ መሰራቱም ተገልጿል፡፡
የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥን በማሳደግ በከተማና በሀገር አቀፍ ደረጃ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት መቻሉም ተጠቁሟል።
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በሚኒስቴሩ እና በተጠሪ ተቋማት በኩል የተከናወኑ የዘርፉ ሥራዎች ለሀገሪቱ ትላልቅ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ገልጸዋል።
የሚኒስቴሩ እና የተጠሪ ተቋማቱ አጠቃላይ የዘጠኝ ወራት አፈፃፀሙ የላቀ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ቀሪ ሥራዎች በበጀት ዓመቱ ቀሪ ወራት እንዲሰሩ አቅጣጫ መስጠታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።