Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በተማሪዎችና መምህራን የሚሰሩ የፈጠራ ስራዎች ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲደርሱ ድጋፍ ይደረጋል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተገኙበት 10ኛው ከተማ አቀፍ የተማሪዎችና የመምህራን የሳይንስና የፈጠራ ስራ አውደ ርዕይ ተከፍቷል።

አውደ ርዕዩ “በፈጠራ ስራ የተካነ ትጉህ ትውልድ ለሀገር ብልጽግና” በሚል መሪ ሐሳብ ለሦስት ቀናት በወዳጅነት አደባባይ የሚካሄድ ሲሆን÷ በከተማዋ ከሚገኙ የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች በተውጣጡ ተማሪዎችና መምህራን የተሰሩ የፈጠራ ስራዎች ለዕይታ ቀርበዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአውደ ርዕዩ መክፈቻ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት÷ የተለያዩ ችግር ፈቺ የሆኑ የፈጠራ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ገልጸው፤ የፈጠራ ስራ ከፍ ወዳለ ደረጃ እንዲሸጋገር ማበረታታት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከተማ አስተዳደሩ በተማሪዎችና መምህራን የሚሰሩ የፈጠራ ስራዎች ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲደርሱ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስገንዝበዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ አውደ ርዕዩ የሚሰሩ የፈጠራ ስራዎች የደረሱበትን ደረጃ ለህብረተሰቡ ከማስተዋወቁ ባሻገር የፈጠራ ባለቤቶቹን ለተሻለ ስራ የሚያነሳሳ መሆኑን ተናግረዋል።

የከተማዋ ነዋሪዎችም ለዕይታ ክፍት በሆነው አውደ ርዕይ በመገኘት የፈጠራ ባለቤቶቹን እንዲያበረታቱ ጥሪ ማስተላለፋቸውን የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ መረጃ ያመላክታል።

Exit mobile version