አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኮሪደር ልማት ሥራዎችን በተሻለ ቅንጅት ለማከናወን አቅም ተፈጥሯል ሲሉ የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 26ኛ መደበኛ ስብሰባ የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴርን የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም አዳምጧል፡፡
ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ ለምክር ቤቱ እንዳብራሩት፤ በኮሪደር ልማት የመንገድ መሰረተ ልማት፣ የመኪና ፓርኪንግ፣ የልጆች መጫወቻ ስፍራዎች፣ የሕዝብ መጸዳጃ ቤቶች፣ የመስመር ዝርጋታ ሥራዎችን በተሻለ ቅንጅት ለማከናወን አቅም ተፈጥሯል።
መንግስት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የምጣኔ ሃብት እና የማህበራዊ ዕድገት ዘላቂነት እና ፍትሃዊነት ለማረጋገጥ የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ፣ ጥገና እና እንክብካቤ ሥራን ቀጣይነት ባለው መልኩ እያካሄደ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል፡፡
የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶችን በስታንዳርዱ መሰረት በመስጠት የዜጎችን እርካታ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 14 ከተሞች የተዘጋጁ ስታንዳርዶችን መተግበራቸውን ተናግረዋል።
በዚህም የትግበራ ሽፋኑን ወደ 220 ከተሞች ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔትን በማስፋፋት በከፋ ድህነት የሚገኙ የከተማ ዜጎችን የኑሮ ሁኔታ እና የሚኖሩበትን አካባቢ ማሻሻል የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
በምክር ቤቱ የከተማ፣ መሰረተ ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ እሸቱ ተመስገን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የከተማ ኮርደር ልማት ሥራዎች ከአዲስ አበባ ተሞክሮ በመውሰድ በሌሎች ከተሞችን ወደ ትግበራ ምዕራፍ መሸጋገሩን ገልጸዋል።
የከተማ መሬት አስተዳደር ካዳስተር ስርዓት መሬት በሚፈለገው አገልግሎት ለተጠቃሚዎች በማቅረብ ረገድ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆኑን መጠቆማቸውን የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል።