የሀገር ውስጥ ዜና

ሰብዓዊ ድጋፍን በዘላቂነት በራስ አቅም ለመሸፈን ስኬታማ ሥራ እየተሰራ መሆኑ ተመላከተ

By ዮሐንስ ደርበው

April 25, 2025

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሰብዓዊ ድጋፍን በዘላቂነት በራስ አቅም ለመሸፈን በሁሉም ክልሎች ስኬታማ ሥራ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ገለጹ።

ኮሚሽነሩ ኢትዮጵያ ሰብዓዊ ድጋፎችን በራስ አቅም በማሟላት ከተረጂነት ለመላቀቅ የምታከናውነውን ተግባር አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፤ በሀገሪቱ በግብርና ዘርፍ እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶች ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን መቋቋም የሚያስችል አቅም እየፈጠሩ እንደሚገኙ አንስተዋል፡፡

መንግሥት የኢትዮጵያን የተረጂነት ታሪክ ለመቀየር ልዩ ትኩረት መስጠቱን ጠቁመው፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ20 ሚሊየን በላይ ዜጎች የተሳተፉበት ውይይት በማድረግ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም መሸፈን እንደሚቻል መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሰፊ የሚታረስ መሬት፣ የውሃ ሃብት እና በርካታ የተማረ ሰው ሃይል ያላት ሀገር መሆኗም የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ትልቅ አቅም መሆኑን አንስተዋል፡፡

የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ብሔራዊ ደህንነትን የማስጠበቅ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም በመሸፈን የሀገር ክብርን ለማስጠበቅ እየተጋን ነው ብለዋል።

መግባባት፣ መዘጋጀት እና በተቀናጀ መንገድ የልማት ስራን ማፋጠን ተረጂነትን ለማስወገድ ወሳኝ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

በዚህ መርህ መሰረት ብሔራዊ የመጠባበቂያና የዕለት ደራሽ የምግብ ክምችትን ለማሟላትም በሁሉም ክልሎች ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል።

የእስከ አሁን እንቅስቃሴም ትልቅ ስኬት እየተመዘገበበት ነው ብለዋል።

ተረጂነትን ሙሉ ለሙሉ ማስቀረት እንደሚቻል በበጋ መስኖ ስንዴ፣ በሌማት ትሩፋትና በኢንዱስትሪ ዘርፎች እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶች ማሳያ መሆናቸውንም አብራርተዋል፡፡

በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይጸድቃል ተብሎ የሚጠበቀው የአደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ ለሰውሰራሽና ለተፈጥሯዊ አደጋዎች በራስ አቅም ምላሽ የመስጠት አቅምን እንደሚያጎለብትም አስገንዝበዋል፡፡

ይህም የውጭ እርዳታ ጥገኝነትን በማስቀረት ሰብዓዊ ድጋፍን በዘላቂነት በራስ አቅም ለመሸፈን እና የተሟላ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እንደሚያስችል ነው ያስረዱት፡፡