አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች ዜጎችን ተጠቃሚ ከማድረግ ባሻገር የመዲናዋን የዲፕሎማሲ ከተማነት የሚያጠናክሩ መሆናቸውን የተቋማት የስራ ኃላፊዎች ገለፁ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የማህበራዊ ዘርፍ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስተባባሪነት በመዲናዋ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸው ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመረቀውን የካዛንቺስ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ የአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል፣ የእንስሳት ልማትና ልህቀት ማዕከል፣ የገላን ጉራ የተቀናጀ የመኖሪያና የልማት መንደር እንዲሁም የጫካ ፕሮጀክትን ተመልክተዋል፡፡
የሥራ ኃላፊዎቹ በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች ሁሉን አቀፍ መሆናቸውን ገልጸው ልማቶቹ ዜጎችን በጤና፣ በባህልና ስፖርት እንዲሁም በማህበራዊ ዘርፍ ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪም የከተማዋን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ እየተከናወኑ የሚገኙ ሁሉን አቀፍ የልማት ስራዎችን በተግባር መመልከታቸውን ተናግረዋል።
የልማት ስራዎቹ ዜጎችን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ የሀገርን ገፅታ የሚገነቡና ከተማዋ የአፍሪካ መዲናነቷን የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ገልዋል።
በተጨማሪም ባህልን፣ ስፖርትንና ኪነጥበብን ሊያሳድጉ የሚችሉ መሰረተ ልማቶችን ያካተቱ በመሆናቸው ዘርፎቹን ለማሳደግ እንደሚያስችሉ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡