Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የመከላከያ ሠራዊት ባስመዘገባቸው ድሎች ሳይኩራራ ለበለጠ ተልዕኮ ራሱን ማዘጋጀት ይገባዋል – ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በወቅታዊ ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊ፣ ቀጣናዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ለከፍተኛ የመከላከያ ሠራዊት አመራሮች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በተመዘገቡ ሁለንተናዊ ድሎች ሳንዘናጋ ለበለጠ ድል መትጋት ይገባል ብለዋል።

ታላቁን የህዳሴ ግድብ በከፍተኛ ፈተናዎች ውስጥ ገንብተን በማጠናቀቅ ሀገርና ህዝብን አንገት ከማስደፋት ለማዳን የተቻለበትና የጠላቶቻችን የተቀናጀ ሴራ ያከሸፍንበት አንዱ ማሳያ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ሀገራዊ ኢኮኖሚያችን ፈተናዎችን በመቋቋም በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉንም ዓለም አቀፍና ሀገራዊ መረጃዎችን በማጣቀስ አብራርተዋል።

ባለፉት ዓመታት ብዙ ሀገራት በዲፕሎማሲው መስክ በትብብር ለመስራት ፍቃደኝነታቸውን ማሳየታቸውንና ይህንን በጎ ዕድል በመጠቀም የብሄራዊ ጥቅማችን ለማሳካት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ለማረጋገጥና የባህር በር ተጠቃሚ ለመሆን የቀረበው ጥያቄ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ፍትሃዊ አጀንዳ ሆኖ መያዙንም ገልፀዋል።
ተለዋዋጭና ኢ-ተገማች በሆነው ዓለም አቀፋዊና ቀጠናዊ እንቅስቃሴ ያለንን ሁለንተናዊ ዝግጁነት በማረጋገጥና የተለያዩ ስልቶችን በመንደፍ ተጋላጭነታችንን ለመቀነስ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝም አመላክተዋል።

በተከተልነው የሰላም ስምምነት የፀና ወታደራዊ ድል ተመዝግቧል ያሉት ጌዲዮን (ዶ/ር)÷ የሚያጋጥሙ ውስጣዊ ችግሮችን በሰላምና በይቅርታ በመፍታት በሀገርና በህዝብ ላይ የሚደርሰውን ጥፋት ለመቀነስ መንግስት እየወሰደው ያለው በሳል እርምጃ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቡን ተናግረዋል።

የመከላከያ ሠራዊቱ ከሌሎች የፀጥታ ሀይሎች ጋር በመሆን በፅንፈኞች ላይ በወሰደው እርምጃ ለሀገርና ለህዝብ ስጋት ከመሆን ወርደው የራሳቸውን ህልውና ለማቆየት እየተቸገሩ መምጣታቸውን አንስተዋል።

ሠላምን ለማፅናትና ብልፅግናንን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ ገልፀው÷ የመከላከያ ሠራዊቱ ባስመዘገባቸው ድሎች ሳይኩራራ ለበለጠ ተልዕኮ ራሱን ማዘጋጀት ይገባዋል ማለታቸውን የመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ አመላክቷል።

በውይይቱ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላን ጨምሮ ከፍተኛ የሠራዊቱ አመራሮች ተገኝተዋል።

Exit mobile version