Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የተሰለፈበትን ዓላማ የተረዳ ብሄራዊ የመከላከያ ሠራዊት ተገንብቷል – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሁለንተናዊ መስክ ራሱን እያበቃ የመጣና የተሰለፈበትን ዓላማ ጠንቅቆ የተረዳ ሀገሩን የሚወድ ፕሮፌሽናል ሠራዊት መገንባቱን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ፡፡
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከሠራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይት÷ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተቋሙ የተሰራው ሪፎርም በርካታ ውጤቶች ለማስመዝገብ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አንስተዋል።
ሀገራችን በታሪኳ በዚህ ደረጃ ብዛትና ጥራት ያለው የፕሮፌሽናል ሰራዊት ገንብታ አታውቅም ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ፥ ሀገሩንና ሙያውን የሚወድ የሚሰጠውን ግዳጅ በአነስተኛ ኪሳራ የመፈፀም ብቃት ያለው ኃይል ተገንብቷል ብለዋል።
ሠራዊቱ ሀገርን ከብተና ከማዳን ባለፈ የሀገሪቱን ሰላም፣ ብልፅግናና ዲሞክራሲን ለማረጋገጥ እየተደረገ ባለው ጥረት ያስመዘገባቸው ድሎች በታሪክ ሲዘከር የሚኖር መሆኑን ተናግረዋል።
በተገኙ ድሎች ባለመኩራራት የተመዘገቡ ሁለንተናዊ ድሎችን አጠናክሮ ለማስቀጠልና የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በተሳሳተ ስሌት ወደጫካ ገብተው የነበሩ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎች የሰላምን መንገድ በመከተል እጃቸውን ለሠራዊቱ መስጠታቸውንም ተናግረዋል፡፡
በተለያየ ቦታ ይንቀሳቀሱ የነበሩ ፅንፈኞች ከመቼውም ጊዜ በላይ መዳከማቸውን የገለጹት ኤታማዦር ሹሙ፥ የሰላምን ጥሪ ያልተቀበሉትን የመለቃቀም ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።
በጦር ሜዳ ማሸነፍ ያቃታቸው የሀገርና የህዝብ ጠላቶች የውሸት ትርክት በመፍጠርና የሥነልቦና ጦርነት በመክፈት ሰራዊቱን ለማጠልሸት ቢሞክሩም በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ማጣታቸውንና ህዝቡ ለሰራዊቱ የሚያደርገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።
በምድር፣ በባህር፣ በአየርና በሳይበር ኃይል የተደራጀው ሠራዊቱ ዘመኑ የደረሰበት የቴክኖሎጂና የውጊያ አቅም ላይ ለማድረስ መቻሉንም ገልጸዋል፡፡
በተሳሳተ ስሌት ውጊያ ለመክፈት የሚሞክሩ ኃይሎችን በአነስተኛ ኪሳራና በአጭር ጊዜ ለመደምሰስ ሰራዊቱ ዝግጁ ነው ማለታቸውንም ከሰራዊቱ ማኅበራዊ ተስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
Exit mobile version