አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ የተመራ ከፍተኛ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) ምክትል ማኔጂንግ ዳይሬክተር ናይጄል ክላርክ ጋር ተወያይቷል።
በኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አፈጻጸም ላይ የተወያዩ ሲሆን በሚያዝያ 2025 መጀመሪያ ላይ በኢትዮጵያ የተካሄደውን ሶስተኛውን የአይ ኤም ኤፍ ፕሮግራም ግምገማ ተልዕኮ ግኝቶችን ተመልክቷል።
አቶ አህመድ ሺዴ ማሻሻው የኢትዮጵያን የለውጥ አጀንዳ ወደ ፊት ለማራመድ ኢኮኖሚውን በመክፈት እና በማዘመን፣ አዳዲስ የእድገት እድሎችን በመፍጠር የሀገሪቱን ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ አቅም ለማስፋት እና የስራ ዕድል ለመፍጠር ትልቅ ሚና እንደነበረው ገልጸዋል።
ናይጄል ክላርክ በበኩላቸው በጠንካራ ማሻሻያ መርሃ ግብር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ፈታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩም ቁልፍ የሆኑ የማክሮ ኢኮኖሚ ግቦችን በማሳካት ላይ ያለውን እድገት፣ የገቢ ማሰባሰብን እና የንግድን ሁኔታ ማሻሻልን እንዲሁም ሌሎችንም ስራዎች አድንቀዋል፡፡
የኢትዮጵያን እድገትና ዘላቂ ልማት በፍጥነት ለማስቀጠል የሚረዳውን የሪፎርም እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ የቅርብ ትብብር እና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ለማድረግ ተቋማቸው ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡