አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ፖሊስ የተመሰረተበት 116ኛ ዓመት በዓል አስመልክቶ የሚካሄደው 5ኛው የምሥራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅት አባል ሀገራት የስፖርት ውድድር ተጀምሯል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውድድሩን ማስጀመራቸውንና የአፍሪካውያን ሰላም፣ ዕድገት እና ብልጽግና ያለ ፖሊስ ተቋማት ጥንካሬ ብሎም ብቃት የሚታሰብ አለመሆኑን በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዘመናዊ የፖሊስ ተቋምን ከአንድ ምዕተ ዓመት በፊት በመመስረት ግንባር ቀደምና ተምሳሌት ሀገር መሆኗንም አውስተዋል፡፡
ባለፉት ሰባት ዓመታት ያደረግነው የጸጥታ ተቋማት ሪፎርም ደግሞ፤ ፖሊስን በይበልጥ ዘመናዊ፣ ዝግጁ፣ ደረጃውን የጠበቀ እና ግዳጅ ፈጻሚ እያደረገው ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፖሊስ ኢትዮጵያንና አፍሪካን በዓለም መድረክ ያስጠሩ ስመ ጥር ስፖርተኞችን ያፈራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
እንዲህ ዓይነት አፍሪካዊ የሆኑ ስፖርታዊ ኩነቶችን እንዲያዘጋጅ ታሪኩም ልምዱም ይረዳዋል ያሉት አቶ ተመስገን፤ አፍሪካውያን አፍሪካን በሚመጥን ደረጃ ተባብረን መሥራት አለብን ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
በየአካባቢያችን ያለንን ዕውቀት፣ ልምድ፣ ቴክኖሎጂና ብቃት ደምረን ከተጠቀምን፤ የተሻለ የፖሊስ ተቋም የመገንባት ሕልማችንን እውን ማድረግ እንችላለን ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
የምሥራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅትም ይህንን ፖሊሳዊ ኅብረትና ወዳጅነት ያጠናክራል ብለዋል፡፡
ውድድሩ ለአንድ ዓላማ ተቀራርቦ የመሥራት ባህልን ያዳብራል፤ ይህ የስፖርት ፌስቲቫል ኅብረታችን የበለጠ የሚጠናከርበት ይሆናል ነው ያሉት፡፡