ፋና ስብስብ

የሀገር አቀፍ እና የፌዴራል ባለድርሻ አካላት የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ መለያ ባህሪያት

By Adimasu Aragawu

April 28, 2025

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ)የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አጀንዳን ከሚያሰባስብባቸው መንገዶች አንዱ ህዝባዊ ውይይቶች እንደሆኑ ይታወቃል፡፡

በእስካሁኑ ሂደት ኮሚሽኑ በ11 ክልሎች እና 2 የከተማ አስተዳደሮች የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍን ሲያከነውን መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡

በሂደቱ በክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የአጀንዳ ሀሳቦቻቸውን ሰጥተዋል፡፡

በቀጣይም ኮሚሽኑ በሀገር አቀፍ እና በፌዴራል ደረጃ ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት አጀንዳን ይሰበስባል፡፡

ታዲያ ይህ ሂደት ከዚህ ቀደም ሲደረጉ ከነበሩ የክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች የአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር ምዕራፍ በምን ይለያል የሚለውን ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ሲሆን የሚከተሉት ሀሳቦች ይህንኑ ይብራራሉ፡፡

👉ምህዳርን ማስፋት የሀገር አቀፍ እና የፌዴራል ባለድርሻ አካላት የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚገኙ ማህበራትን እና ተቋማትን በማሳተፍ በሌላ እርከን ያልተዳሰሱ ተጨማሪ የአጀንዳ ሀሳቦችን ለማግኘት ያስችላል፡፡

👉 የአጀንዳ ሀሳቦች ተፈጥሮ ማሰባጠር የአጀንዳ ሀሳቦችን ቅርፅ ስናይ በክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች በተደረገው አጀንዳን የማሰባሰብ ሂደት የቀረቡ አጀንዳዎች ሀገራዊ ፍይዳቸው ያላቸው አጀንዳዎች መቅረባቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ክልላዊ ይዘት ያላቸው አጀንዳዎችም ሲቀርቡ ተስተውሏል፡፡ በሀገር አቀፍ እና በፌዴራል ባለድርሻ አካላት የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት የሀገርን ህልውና እና አንድነት መሰረት በማድረግ ለፖሊሲ ግብዓት ሊጠቅሙ የሚችሉ መሰረታዊ የአጀንዳ ሀሳቦች እንደቀርቡበት ይጠበቃል፡፡

👉ተሳታፊነትን ማረጋገጥ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ውክልናን መሰረት ያደረገ ሂደት እንደመከተሉ መጠን በክልሎች/ከተማ አስተዳደሮች የአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር ምዕራፍ ላይ አጀንዳዎቻቸውን እንዲሰጡ ዕድሉን ያላገኙ አካላት ሊኖሩ እንዲሚችሉ ይታመናል፡፡

ይህንን ከግምት በማስገባት ሁሉም አካላት ተቋማዊ መብቶቻቸውን በመጠቀም ስለሀገራቸው ኢትዮጵያ የአጀንዳ ሀሳቦቻቸውን እንዲያቀርቡ ይህ ሂደት ተመቻችቶላቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ እየመከረች ነው!