አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሥራ በሆነው የመደመር ትውልድ መጽሐፍ ሽያጭ ገቢ እየተገነባ የሚገኘው የድሬዳዋ አሥተዳደር የመደመር ትውልድ ቤተ-መጻሕፍት ግንባታን በሦስት ወራት ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ፡፡
ቤተ-መጻሕፍቱ የንባብ ባህልን ለማጎልበት ብሎም በሥነ-ምግባርና በዕውቀት የታነፀ ትውልድን ለማፍራት የጎላ ሚና እንዳለው የድሬዳዋ አሥተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚካኤል እንዳለ ገልፀዋል፡፡
ከ470 ሚሊየን ብር በሚልቅ ወጪ እየተገነባ ያለው ቤተ-መጻሕፍቱ፤ አሁን ላይ የግንባታ አፈጻጸሙ 80 በመቶ መድረሱን ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል፡፡
አጠቃላይ ግንባታው በ2 ሺህ ካሬ ማረፉን፣ ቤተ-መጻሕፍቱ ባለ አራት ወለል ሕንጻ መሆኑን፣ በውስጡም የማንበቢያ ሥፍራ፣ የመዝናኛ ቦታ እንዲሁም የአካል ጉዳተኞች ማንበቢያና መገልገያ ቦታ ያካተተ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በአንድ ጊዜ ከ1 ሺህ በላይ ሰዎችን የማስተናገድ ዐቅም እንዳለውም አስታውቀዋል፡፡
በቲያ ኑሬ