አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከ52 ሺህ በላይ የአዕምሯዊ የፈጠራ ውጤቶችን መመዝገቡን የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
ዓለም አቀፍ የአዕምሯዊ ንብረት ቀን ለ25ኛ ጊዜ “ሙዚቃና አዕምሯዊ ንብረት” በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ ሥነ-ሥርዓቶች በመከበር ላይ ይገኛል።
ቀኑን የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ከፈጠራ ባለመብቶች፣ ባለድርሻ አካላትና አጋር ተቋማት ጋር በመሆን በሳይንስ ሙዚየም በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበረው ነው የሚገኘው።
የባለስልጣኑ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ኃላፊ ኤልያስ መሃመድ፤ በ3 ዘርፎች ማለትም በቅጅና ተዛማጅ፣ በፓተንት (በፈጠራ) እንዲሁም በንግድ ምልክት ዘርፎች ከ52 ሺህ 500 በላይ የአዕምሯዊ የፈጠራ ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።
በንግድ ምልክት ዘርፍ የምዝገባ ሂደት ወቅት የማህበረሰቡን ወግና ባህል የማይጥሱ፣ ከሌሎች የንግድ ምልክቶች ጋር የማይመሳሰሉ እንዲሁም ሸማቹን ግራ የማያጋቡና ልዩ መሆን አንዱ የፈጠራ ውጤት መስፈርት መሆኑን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በፓተንት ዘርፍ ዕውቅና ለማግኘት የፈጠራ ስራው አዲስ፣ ተግባራዊ የተደረገ ብሎም የፈጠራ ብቃቱ መረጋገጥ አለበት ነው ያሉት።
የፈጠራ ስራን አለማስመዝገብ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል ያሉት ኃላፊው÷ ይህም ለኢኮኖሚያዊ እና የሞራል ኪሳራ ሊዳርጋቸው እንደሚችል አስረድተዋል።
አዲስ አበባ ውስጥ ብቻ ካለው የነጋዴ ብዛት አንጻር የተመዘገበው የንግድ ምልክት ዝቅተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህ ደግሞ የግንዛቤ ክፍተት አንዱ ችግር መሆኑን ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል።
የንግድ ምልክት በራሱ አንድ ሃብት መሆኑን ገልጸው÷ ሁሉም የፈጠራ ባለቤቶች ስራዎቻቸውን እንዲያስመዘግቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየሰራን እንገኛለን ብለዋል፡፡
በመሳፍንት እያዩ