Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ፈጣን የከርሰ ምድር ውሃ ሀብት ጂኦፊዚካል ጥናት ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል ፈጣን የከርሰ ምድር ውሃ ሀብት ጂኦፊዚካል ጥናት ፕሮጀክት ይፋ ሆኗል፡፡

ለ5 ዓመት የሚተገበረውን ፕሮጀክት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከዴንማርክ መንግስት ጋር በመተባበር ነው ይፋ ያደረገው።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) በዚሁ ወቅት÷ ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ ያላትን የከርሰ ምድር የውሃ ሀብት በመጠን፣ በጥራትና መገኛ ቦታን ጨምሮ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።

ከአሁን በፊት ኢትዮጵያ ያላት የከርሰ ምድር የውሃ ሀብት በመጠንና በጥራት የተደገፈ መረጃ እንዳልነበረውም አመላክተዋል።

በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሳደር ሱኔ ክሮግስትረፕ በበኩላቸው÷ ፕሮጀክቱ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን እና የአየር ንብረት ለውጥን ይደግፋል ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ዘመናዊ የጂኦፊዚካል ቴክኖሎጂዎችን በኢትዮጵያ የውሃ ዘርፍ ላይ ተግባራዊ በማድረግና በማሳደግ የከርሰ ምድር የውሃ ሀብቶች አቅምን በማዳበር ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የውሃ ሀብት አስተዳደርን ለመደገፍ ያለመ መሆኑን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።

Exit mobile version