ዓለምአቀፋዊ ዜና

ቭላድሚር ፑቲን የሩሲያን የድል ቀን አስመልክተው የተኩስ አቁም አወጁ

By Mikias Ayele

April 28, 2025

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የሩሲያን የድል ቀን አስመልክተው የሶስት ቀናት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጀዋል፡፡

ከሬምሊን እንዳስታወቀው÷ጊዜያዊ የተናጠል ተኩስ አቁሙ በፈረንጆቹ ከመጪው ግንቦት 8 እኩለ ሌሊት ጀምሮ እስከ ግንቦት 11 ቀን ይቆያል፡፡

በዚህ መሰረትም በተጠቀሱት ቀናት በሁሉም የውጊያ ግንባሮች የሚገኙ የሩሲያ ወታደራዊ ክፍሎች ምንም አይነት ተኩስ እንደማያደርጉ ተመላክቷል፡፡

ይሁን እንጂ ዩክሬን የተኩስ አቁሙን በመጣስ ትንኮሳ የምትፈጽም ከሆነ ሩሲያ አስፈላጊውን አጸፋ እንደምትሰጥ ነው ፕሬዚዳንቱ የተናገሩት፡፡

ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ዘላቂ የተኩስ አቁም ንግግር ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗንም አረጋግጠዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ፑቲን የዩክሬን መንግስት ተመሳሳይ የተኩስ አቁም እንዲያውጅ ጥሪ ማቅረባቸውንም አር ቲ ዘግቧል፡፡

የቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት የናዚ ጀርመኖችን በፈረንጆቹ 1945 ድል ያደረገችበት የድል በዓል በሞስኮ በየዓመቱ ግንቦት 9 ቀን በተለያዩ ወታደራዊ ትርዒቶች ይከበራል፡፡