አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ዓለም ባንክ የኢትዮጵያ መንግስት ተግባራዊ ያደረገውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያና ተግባራዊ ለማድርግ ያሳየውን ቁርጠኝነት አድንቋል፡፡
በገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ የተመራ ከፍተኛ የፋይናንስ ልዑክ ከዓለም ባንክ የኦፕሬሽን ክፍል ማኔጂንግ ዳይሬክተር አና ቢየርድ ጋር የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራውን በተመለከተ ውይይት አድርጓል፡፡
በውይይቱ ሁለቱ ወገኖች የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ መንግስትን የልማት አጀንዳዎች እንዲሁም በቀጣናዊ የልማት ዘርፎች ላይ የሚያደርገውን ድጋፍ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ምክክር አድርገዋል፡፡
አቶ አህመድ ሽዴ በዚህ ወቅት÷ ዓለም ባንክ በኢትዮጵያ የልማት ግቦች እና የሪፎርም አጀንዳዎች ላይ እያደረገ ያለውን የፋይናንስ እና ቴክኒካል ድጋፍ አድንቀዋል፡፡
ተቋሙ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ፣ የግሉን ዘርፍ ኢንቨስትመንት ለማጎልበት፣ በስራ አድል ፈጠራ እና በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገት ዘርፎች እያደረገ ላለው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
አና ቢየርድ በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ መንግስት የማክሮ ኢኮኖሚ ግቦችን ለማሳካት ያሳየውን ቁርጠኝነት በማድነቅ÷ እንደ ወርቅ ያሉ የወጪ ምርቶች እንዲጨምሩ በማድረግ የተሻለ የገቢ አሰባሰብ እንዲኖርና ምቹ የንግድ ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
ባለፉት 9 ወራት መንግስት በወሰደው የማክሮ ኢኮኖሚ አስተዳደር እና የማሻሻያ እርምጃዎች ፈታኝ በሆነው ዓለም አቀፍ ሁኔታ በኢትዮጵያ የማይበገር ኢኮኖሚ መገንባት መቻሉንም ተናግረዋል፡፡
ማሻሻያው በኢትዮጵያ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተገነቡ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች አዎንታዊ አፈፃፀም እንዲኖራቸው አደርጓልም ብለዋል፡፡
ከዓለም ባንክ እና አይ ኤም ኤፍ ዓመታዊ ስብሰባ ጎን ለጎን በተካሄደው ውይይት÷ ሁለቱ ወገኖች የኢትዮጵያን እድገት እና የዘላቂ ልማት ጉዞ ለማፋጠን በትብብር መስራት አስፈላጊ መሆኑን አፅንዖት መስጠታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡