አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በከተማ አስተዳደሩ የተከናወኑ የዘጠኝ ወራት የጸጥታ ስራዎችን ገምግመዋል።
ከንቲባዋ በዚሁ ወቅት የከተማዋን እድገትና ለውጦች የሚመጥኑ የጸጥታ ስራዎች በመሰራታቸው ከተማዋን ሰላማዊ፣ የተረጋጋችና ለመኖር ምቹ በማድረግ ረገድ ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል፡፡
ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር የጸጥታ ስጋት ሊሆኑ የሚችሉ እንቅስቃሴዎችን ቀድሞ በመለየት፣ ህዝቡን በቀጥታ በማሳተፍና ወንጀል በመከላከል በርካታ ስራዎች መሰራታቸውንም ተናግረዋል፡፡
በግምገማ መድረኩ ላይ የተካፈሉ የጸጥታ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች በበኩላቸው፥ የከተማ አስተዳደሩ ለፀጥታ አካላት እያደረገ ያለው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ትልቅ የሞራል ስንቅ እንደሆናቸው ገልጸዋል፡፡
በከተማዋ የወንጀል መከላከልና የመቆጣጠር አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልጸው፥ ህብረተሰቡ በሰላም ሰራዊት በመደራጀት ከፌደራልና ከከተማዋ የጸጥታ መዋቅር ጋር በቅንጅት በመስራቱ ውጤት መገኘቱንም ተናግረዋል።
ከንቲባዋ በመጨረሻም የጸጥታ ተቋማት ከተማዋን ከተደራጀ የዝርፊያና ከየትኛውም የፀጥታ ስጋት የፀዳች በማድረግ ህብረተሰቡን በማሳተፍ የተገኙ ለውጦችን አጠናክረው እንዲያስቀጥሉ ማሳሰባቸውን ከከንቲባ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡