አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት ከአጋር ሀገራት ጋር በትብብር እየሰራች መሆኗን የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለፀ፡፡
ሚኒስቴሩ ከፈረንሳይና ከሱዳን ሪፑብሊክ ምሁራን ጋር የዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ስርዓትን ለማጎልበት የሚያስችል አውደ ጥናት እያካሄደ ይገኛል፡፡
አውደ ጥናቱ በሀገራት መካከል በትምህርት መስክ ቀጣይነት ያለው የኢኖቬሽን፣ ቴክኖሎጂና የዲጂታል እውቀት መጋራትና የልምድ ልውውጥን በማሳለጥ የዲጂታል ኢኮኖሚውን በጋራ ለመገንባትና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በአውደ ጥናቱ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሹሩን ዓለማየሁ (ዶ/ር)÷ ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚውን ለመገንባት በሚያስችሉ የትምህርት አካዳሚክ ዘርፍ ላይ ከአፍሪካና ከሌሎች አጋር ዓለም ሀገራት ጋር በትብብር እየሰራች መሆኗን ገልጸዋል።
ከፈረንሳይ የትምህርት ተቋማት በተውጣጡ ምሁራንና እና ከሱዳን ዩኒቨርሲቲ ምሁራንና ከፍተኛ ባለሙያዎች ጋር ዘርፉን ለማሳደግ የሚሰሩ የዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ለማጎልበት የሚካሄደው አውደ ጥናት ለሀገራቱ የላቀ ሚና እንዳለው መናገራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡
ለሦስት ቀናት በሚቆየው አውደ ጥናት ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ከፈረንሳይ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተልዕኮ ምሁራን እና ከሱዳን ሪፑብሊክ ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የተውጣጡ ምሁራን እና ተመራማሪዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡