የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ የባለብዝሃ ወገን የትብብር ማዕቀፍ ለማጠናከር ተስማሙ

By Mikias Ayele

April 28, 2025

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ የሁለትዮሽ የልማት አጋርነታቸውን በተለያዩ የትብብር አማራጮች የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰሩ አስታወቁ።

በገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ የተመራ ከፍተኛ ልዑክ ከዓለም ባንክ ግሩፕ እና አይ ኤም ኤፍ ዓመታዊ የፀደይ ወቅት ስብሰባ ጎን ለጎን ከፈረንሳይ የኢኮኖሚ እና ፋይናንስ ሚኒስቴር የባለብዙ ወገን ጉዳዮች እና ልማት ረዳት ፀሐፊ ዊሊያም ሮስ ጋር ተወያይቷል።

አቶ አሕመድ ሽዴ በዚህ ወቅት÷ ፈረንሳይ ለኢትዮጵያ በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን ማዕቀፎች እያደረገች ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

ፈረንሳይ ከቻይና ጋር በጋራ ሊቀ-መንበርነት በምትመራው የኢትዮጵያ የአበዳሪዎች ኮሚቴ በቡድን 20 አባል ሀገራት የዕዳ ማቃለያ ማዕቀፍ የኢትዮጵያ የእዳ አስተዳደር ድርድሮች ላይ ድጋፏን እየሰጠች መሆኗንም አንስተዋል።

ሚኒስትሩ ለዊሊያም ሮስ የኢትዮጵያን የሪፎርም ትግበራ እና የኢትዮጵያ መልካም የኢኮኖሚ አዝማሚያ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ፈተናዎችን አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።

የፈረንሳይ የኢኮኖሚ እና ፋይናንስ ሚኒስቴር የባለብዙ ወገን ጉዳዮች እና ልማት ረዳት ፀሐፊ ዊሊያም ሮስ በቡድን 20 አባል ሀገራት የዕዳ ማቃለያ ማዕቀፍ የእዳ አስተዳደርን አስመልክቶ በጽንሰ ሀሳብ ደረጃ ከአበዳሪዎች ጋር የደረሰችውን ስምምነት አድንቀዋል።

የመንግስትን ጠንካራ የማክሮ ኢኮኖሚ አስተዳደር እና የሪፎርም እርምጃዎች መልካም የሚባሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሁለቱ ወገኖች በውይይታቸው የኢትዮጵያ እና ፈረንሳይን የልማት አጋርነት በሁለትዮሽ እና የባለብዝሃ ወገን የትብብር ማዕቀፍ የበለጠ ለማጠናከር መስማማታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።