ቢዝነስ

ኢትዮጵያና የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ በልማት ትብብር ላይ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ተስማሙ

By Melaku Gedif

April 29, 2025

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ከአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንት አምበሮይስ ፋዮሌ ጋር በልማትና ኢንቨስትመንት ትብብር ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል።

የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እና ማህበራዊ እድገት ዙሪያ ተጨባጭ አስተዋጽኦ ከማበርከት አኳያ ጉልህ ሚና ያላቸው ዘርፎች ላይ ለሚያደርገው ቀጣይነት ያለው ድጋፍ አቶ አህመድ ሺዴ ምስጋና አቅርበዋል።

በተለይም በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ፋይናንስ፣ ውሃ፣ የንጽህና አጠባበቅና እና በሴቶች ስራ ፈጠራ ልማት እየተደረገ ላለው ቁርጠኝነትና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ነው ሚኒስትሩ ምስጋና ያቀረቡት።

የባንኩ ምክትል ፕሬዚዳንት በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለኢኮኖሚ ልማትና እድገቷ ቅድሚያ ትኩረት ሰጥታ እያከናወነቻቸው ባሉ ዘርፎች ላይ ሙሉ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

ድጋፉም ለአዲሱ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት በገንዘብ ለመደገፍ ያሉ አማራጮችን ማየትን ጭምር እንደሚያጠቃልል በውይይታቸው ገልጸዋል።

ሁለቱም ወገኖች በቀጣይ ትብብራቸውን ለማጠናከር እንዲሁም የባንኩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በኢትዮጵያ ጉብኝት በሚያደርጉበት ወቅት በተለያዩ ዘርፎችና አማራጮች ላይ ለመወያየት ተስማምተዋል።