Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ከ110 ሺህ በላይ ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች ላይ ርምጃ ተወሰደ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 21፣2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በንግድ ዘርፉ በተከናወኑ በርካታ ሥራዎች ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ የተጠሪ ተቋማት፣ የክልልና የከተማ አስተዳደር የንግድና ገበያ ልማት ቢሮዎች የ9 ወራት አፈጻጸም ግምገማ እየተካሄደ ነው።

ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንደገለጹት÷ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በንግዱ ዘርፍ በተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል፡፡

በቴክኖሎጂ በመታገዝ ለ2 ነጥብ 6 ሚሊየን አገልግሎት ፈላጊዎች የኦንላይን ምዝገባ መከናወኑን ጠቁመው÷ 2 ነጥብ 2 ሚሊየን የንግድ ፍቃድ ኢንስፔክሽን ሥራ መሰራቱንም አንስተዋል።

የቅዳሜና እሑድ ገበያዎችን በማስፋፋት የሲሚንቶ የግብይት ሥርዓት እንዲሁም ሌሎች ተግባራትን በማከናወን አቅርቦት በመጨመር ዋጋው የተረጋጋ እንዲሆን ማስቻሉን ተናግረዋል።

በወጪ ንግድ አፈጻጸም ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል ያሉት ሚኒስትሩ÷ በዚህም በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት 5 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን አመልክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል እንድትሆን የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡

በሌላ በከሉል ከ110 ሺህ በላይ ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች ላይ ርምጃ መወሰዱን ጠቁመው÷ ጠንካራ የነዳጅ ግብይት ቁጥጥር ሥርዓት በመዘርጋት በሕገ-ወጥ የነዳጅ ማደያዎች ላይ ከ100 ሚሊየን ብር በላይ ቅጣት መጣሉን ተናግረዋል፡፡

Exit mobile version