Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ከሩሲያ እና ብራዚል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 21፣2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ከሩሲያ እና ብራዚል አቻዎቻቸው ጋር ተወያይተዋል፡፡
በብራዚል ሪዮ ዲ ጄኔሮ እየተካሄደ በሚገኘው የብሪክስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት ሚኒስትሩ፤ ከስብሰባው ጎን ለጎን የሁለትዮሽ ውይይቶችን አድርገዋል፡፡
ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ከሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር ባደረጉት ውይይት፤ የኢትዮጵያ እና ሩሲያ ሁሉን አቀፍ ግንኙነት መጠናከሩን በማውሳት የሀገራቱን ትብብር ይበልጥ ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሰርጌ ላቭሮቭ በበኩላቸው፤ ሩሲያ በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን የትብብር መስኮች ተጨባጭ ትብብር በማድረግ ታሪካዊ ግንኙነቱን ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።
ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በተመሳሳይ ከብራዚል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማውሮ ቪየራ ጋር ባደረጉት ውይይት፤ ሀገራቱ በምግብ ዋስትና፣ በግብርና ምርታማነት፣ በዓለም አቀፍ የአሥተዳደር ተቋማት ማሻሻያ፣ በኃይል ሽግግርና በሌሎች ዘርፎች ባላቸው ትብብር ዙሪያ መክረዋል።
ብራዚል በብሪክስ የወቅቱ ፕሬዝዳንትነቷ የጀመረችውን ሥራ በማድነቅ፥ ኢትዮጵያ ብራዚል ላስቀመጠቻቸው የብሪክስ የትኩረት አቅጣጫ ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጸዋል።
ሚኒስትሮቹ የሀገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር መስማማታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
Exit mobile version