Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ዩኒቨርሲቲዎች የችግር መፍቻ እንዲሆኑ የአማራ ክልል መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በሁሉም የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ከተመደቡ የአማራ ክልል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አስተባባሪዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ተወያዩ፡፡

የእርስበርስ ጤናማ ግንኙነትን በመፍጠር እና ሰላምና ደኅንነትን በማረጋገጥ ረገድ የአማራ ክልል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አስተባባሪዎች አመርቂ ሥራ እየሠሩ መሆኑን የክልሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አስተባባሪዎች ዋና ዳይሬክተር መልካሙ ታፈሰ ተናግረዋል።

ክልሉ በግጭት ውስጥ መቆየቱን ያነሱት በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ይርጋ ሲሳይ፤ ችግሩን በመቋቋም በክልሉ ውስጥ በሚገኙ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ሰላማዊና ጤናማ የመማር ማስተማር ሥራ መቀጠሉን ገልጸዋል።

በዩኒቨርሲቲዎች ልዩነትን በማስፋት የማጋጨት ሴራ ይዘው የሚንቀሳቀሱ በርካታ ጠላቶች እንዳሉ ጠቁመው፤ በተለይም የብሔር እና የሐይማኖት መልክ የያዙ አጀንዳዎችን በመመከት ውጤታማ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል፡፡

ሰላም ከሌለ መልማት አይቻልም ያሉት አቶ ይርጋ፤ ሁሉም አካል ፀረ-ልማት ሆኖ የሚንቀሳቀስን ማንኛውንም አካል በጋራ ቆሞ መታገል አለበት ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡

በክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችን የችግር መፍቻ ማዕከል በማድረግ ረገድ የክልሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አስተባባሪዎች የሚሰሩትን ሥራም አድንቀዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ሰላማዊ እና የችግር መፍቻ ማዕከል ሆነው እንዲቀጥሉ ቁርጠኛ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡

ክልሉ ሰላም የሰፈነበት እና ልማት የሚፋጠንበት እንዲሆን ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

Exit mobile version