የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴዎች የ22 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር ድጋፍ ለአፋር ክልል አስረከቡ
አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በመዲናዋ የተቋቋመው የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴዎች ያሰባሰቡትን የ22 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር የአይነት እና የገንዘብ ድጋፍ ለአፋር ክልል አስረከቡ።
ኮሚቴዎች ድጋፉን ለአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ያሥረከቡ ሲሆን፥ ድጋፉም በአሸባሪው ቡድን ጉዳት ለደረሰባቸውና ለተፈናቀሉ ወገኖች እንደሚሆን ተገልጿል፡፡
በአዲስ አበባ የተቋቋመው የአፋር ክልል የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ፥ ድጋፉን ከሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ ከሚገኙ የተለያዩ ለጋሽ ባለሀብቶች፣ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ያሰባሰቡት መሆኑም ተመላክቷል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ እና በአዲስ አበባ የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቤ ወይዘሮ ዘሀራ ሁመድ ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት፥ ድጋፉ 12 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር የሚገመት የምግብ፣ የአልባሳት እና የንፅህና መጠበቂያ እንዲሁም በጥሬ ገንዘብ 10 ሚሊየን ብር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
“የደረሰብንን ችግር የምንወጣው በመደጋገፍ ስለሆነ ያደረጋችሁት ድጋፍ ቀላል አይደለም” ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ድጋፉን በተረከቡበት ወቅት መግለጻቸውን ከክልሉ ብዙሀን መገናኛ ድርጅት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
አሸባሪው ቡድን በክልሉ ባደረሰው ጥቃት ጉዳት እና መፈናቀል ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፋ በማሰባሰብ ለሚሳተፉ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!