የአለም ባንክ ለጥራት መሰረተ ልማት ተቋማት የ14 ነጥብ 6 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ አጸደቀ
አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአለም ባንክ አንድ አካል የሆነው ብሔራዊ የጥራት መሠረተ ልማት ፕሮጀክት ለቀጣይ 18 ወራት በጥራት ቁጥጥር ስራ ላይ ለተሰማሩ የጥራት መሠረተ ልማት ተቋማት የ14 ነጥብ 6 ሚሊየን አሜሪካን ዶላር በጀት አጽድቋል፡፡
ፕሮጀክቱ ላለፉት አምስት ዓመታት የጥራት መሠረተ ልማት አገልግሎቶችን ማሻሻል ዓላማ አድርጎ በመስራት በአገልግሎት ሰጪ እና ተቀባይ አካላት መካከል ሚዛናዊ አሰራርን ለመፍጠር ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
ለዚህ ደግሞ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርን ጨምሮ በግሉ ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሃብቶች በርካታ የአቅም ግንባታ እና የመሰረተ ልማት ድጋፎች ሲያደርግ መቆየቱን የጥራት መሠረተ ልማት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስተባባሪ አቶ ወንድወሰን ፍስሃ ተናግረዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በተለይም የምግብ፣ የጨርቃጨርቅ እና የቆዳ ዘርፎች ምርትና አገልግሎት ጥራት ያለው እንዲሆን ትኩረቱን አድርጎ እየሰራ ነው ያሉት አቶ ወንዶሰን፥ ይህንንም እውን በማድረግ በኩል በዘርፎቹ የሚስተዋሉ የምርት ጥራት እና አገልግሎትን ከነበረበት ማሳደግ መቻሉንም ገልጸዋል፡፡
እስካሁን በተደረገው እንቅስቀሴም የጥራት መሠረተ ልማት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል እና አለም አቀፍ እውቅና እንዲኖራቸው በማድረግ በኩል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት።
እ.ኤ.አ ከ2017 ሐምሌ ወር ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገው ይህ ፕሮጀክት ለጥራት መሠረተ ልማት ተቋማቱ አስፈላጊው የአቅም ግንባታ እና የመሰረተ ልማቶች እንዲሟሉ 38 ነጥብ 9 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ ማድረጉንም ጠቁመዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ለቀጣይ አንድ አመት እንደተራዘመ እና የጸደቀው የ14 ነጥብ 6 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር በጀት የጥራት መሠረተ ልማት ተቋማቱ እስከ ሰኔ 30/2015 ዓ.ም ድረስ ለሚያከናውኑት የስራ እንቅስቃሴ የሚውል መሆኑን ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!