Fana: At a Speed of Life!

በሶማሌ ክልል ድርቅን ተቋቁሞ ማለፍ የሚያስችሉ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ተጀመሩ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሌ ክልል ድርቅን ተቋቁሞ ማለፍ የሚያስችሉ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ተግባራዊ መደረግ መጀመራቸውን የክልሉ መንግስት አስታወቀ።
ከዓለም አየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ ከተከሰተው ድርቅ ገፈት ቀማሾች መካከል አርብቶ አደሩ የሶማሌ ማህበረሰብ በጉልህ ይጠቀሳል።
ዘንድሮ በክልሉ ዘጠኝ ዞኖች የሚገኙ 88 ወረዳዎች በተከሰተ ድርቅ አርብቶ አደር የሆነውን የክልሉን ህዝብ ለከፍተኛ ሰብዓዊና ማህበራዊ ቀውስ ዳርጎታል።
ለድርቅ የተጋለጠው ሶማሌ ክልል ዋቢ ሸበሌ፣ ገናሌና ዳዋን የመሳሰሉ ዓመቱን ሙሉ ወራጅ ወንዞች ታድሎ ለምን ውሃ ይጠማል? የቁም እንስሳቱስ በግጦሽ እጦት ለምን ተንከራተቱ? የሚለው የብዙሃኑ ጥያቄ ነው።
በሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ መሀመድ የሱፍ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፥ በክልሉ በየአሥር ዓመቱ ይከሰት የነበረው ድርቅ አሁን ላይ የመከሰት ዕድሉ ወደ ሦስት ዓመት ዝቅ ብሏል።
በመሆኑም የክልሉ መንግስት የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት ድርቅን ተቋቁሞ ማለፍ የሚያስችሉ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን ነድፎ ተግባራዊ በመደረግ ላይ መሆኑን ነው ያስረዱት።
ከፕሮጀክቶቹ መካከልም የገጸ ምድርና ከርሰ ምድር ውሃን አሰባስቦ መጠቀም አንዱ መሆኑን አቶ መሀመድ ጠቅሰዋል።
የክልሉን የውሃ ሃብት ለመስኖ ልማት በማዋል ድርቅን መቋቋም የሚችል ህብረተሰብ ለመፍጠር የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች መነደፋቸውን ገልፀው፥ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከፌዴራል መንግስት ጋር በመተባበር በዘላቂ ልማት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም አውስተዋል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት የተሰሩ ከ200 በላይ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶችም ዘንድሮ የተከተሰውን ድርቅ ለመቋቋም አጋዥ መሆናቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ወራጅ ወንዞችን በመገደብም ሆነ የዝናብ ውሃን በማቆር በክልሉ በሚከናወኑ ሥራዎች የመስኖ ግድቦችን በመጠቀም ለእርሻ ልማት ከማዋል ጎን ለጎን የእንስሳት መኖ ለማልማትም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የውሃ ሀብትን በመጠቀም የሚሰሩ ዘላቂ ልማቶች ድርቅን ከመቋቋም ባለፈ የአርብቶ አደሩን ሕይወት ወደ ከፊል አርብቶ አደርነትና አርሶ አደርነት በማሻገር የኑሮ ዘይቤውን የመለወጥ አቅም እንደሚፈጠር ገልጸዋል።
የሶማሌ ክልል በህወሓት የ27 ዓመታት አገዛዝ በመሰረተ ልማት ሆነ ተብሎ ወደኋላ እንዲቀር መደረጉን አስታውሰው፥ አሁን ላይ ክልሉ ሰላምን ከማረጋገጥ ባለፈ ወደ ልማት ገብቷል ብለዋል።
በመንገድ፣ በመብራት፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በቴሌኮምና በሌሎች መሰረተ ልማት ዘርፎች ባለፉት ሦስት ዓመታት ትላልቅ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ መደረጋቸውንም ገልጸዋል።
ክልሉ ለድርቅ ተጋላጭ ሆኖ ጉዳትን ያስተናገደው በእንስሳት ብቻ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ላይ በመንጠልጠሉ በመሆኑ የህብረተሰቡን የገቢ አማራጮች ማስፋት አብይ ትኩረት ተሰጥቶታል ነው ያሉት አቶ መሀመድ።
የሶማሌ ክልል ሰፊ መልክዓ ምድር የሚያካልል እና ከውጭ አገራት ጋር የሚዋሰንበት ረዥም ድንበር እንዳለው ጠቅሰው የገበያ ትስስር መፍጠርም ሌላው አማራጭ እንደሆነ አንስተዋል።
መሰረተ ልማቶችን ተደራሽ በማድረግ በማዕድን፣ በቱሪዝም፣ በመስኖ ልማትና መሰል የኢኮኖሚ አማራጮችን በማስፋት ከራሱ አልፎ ሌሎችን መጋቢ ክልል ለማድረግ አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል።
በመሆኑም የኑሮ ዘይቤውን በማስፋት ድርቅን ጨምሮ የሚከሰቱ ተፈጥሯዊ አደጋዎችን የሚቋቋም አካባቢ ማድረግ የክልሉ መንግስት ዋነኛ ትኩረት ሆኗል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.