በማኦኮሞ ልዩ ወረዳ በአሸባሪው ሸኔ ተይዘው የነበሩ አካባቢዎችን ማጽዳት ተቻለ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማኦኮሞ ልዩ ወረዳ በተካሄደ የተቀናጀ የሠላምና ፀጥታ ስራ በአሸባሪው ህወሓት ተላላኪ ሸኔ ተይዘው የነበሩ አካባቢዎችን ማጽዳት መቻሉን የክልሉ ሠላም ግንባታ እና ፀጥታ ቢሮ አስታወቀ፡፡
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ሙሳ ሃሚድ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ በልዩ ወረዳው በአሸባሪው ህወሓት ተላላኪ ሸኔ ተይዘው የነበሩ አካባቢዎችን ከሽብር ቡድኑ ማጽዳት የተቻለው ባለፈው አንድ ሳምንት በተካሄደ የተቀናጀ የሠላምና ፀጥታ ስራ ነው።
ምክትል ኃላፊው እንዳሉት፥የአሸባሪው ህወሓት ተላላኪ የሆነው የሸኔ የሽብር ቡድኑ ከሁለት ወራት በላይ በልዩ ወረዳው ተደጋጋሚ ጥቃት በመፈጸም በንጹሃን ዜጎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።
የሽብር ቡድኑ ያደርስ የነበረውን ተደጋጋሚ ጥቃት በመሸሽ በርካታ ነዋሪዎች ከአካባቢው መፈናቃላቸውንም የተናገሩት አቶ ሙሳ፥ ልዩ ወረዳን አስተዳደር ጽህፈት ቤትን ጨምሮ የተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት በአሸባሪው ቡድን መውደማቸውን ገልጸዋል።
ቡድኑ ከአዲስ አበባ ወደ አሶሳ የሚመላለሱ የህዝብ እና የመንግስት ተሽከርካሪዎችን በማስቆም ንጹሃንን አግቶ በመውሰድ እንዲሁም ወደ ክልሉ የሚገቡ ነዳጅ፣ ሸቀጣሸቀጥ እና የምግብ እህል ሲዘርፍ እንደነበር ኃላፊው አስታውሰዋል፡፡
እንዲሁም በልዩ ወረዳው ቶንጎ ከተማ አቅርቢያ የሚገኘው ጎሬ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በሽብርተኛው የሸኔ ቡድን ተዘርፎ ስደተኞች ከአካባቢው መውጣታቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
የሀገር መከላከያ፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የክልሉ ልዩ ኃይልና የአከባቢ ሚሊሻ በቅንጅት ባደረጉት ኦፕሬሽኑ በልዩ ወረዳው ተይዘው የነበሩ አካባቢዎችን ከሽብር ቡድኑ ማጽዳት ተችሏል ብለዋል።
እንደ ምክትል ኃላፊው ገለጻ፥ በልዩ ወረዳው ባለፈው አንድ ሳምንት በተካሄደው የተቀናጀ የሠላምና ፀጥታ ስራ 27 የሽብር ቡድኑ አባላት ሲደመሰሱ፥ 35 ቆስለው ተይዘዋል፤ ሌሎች 13 ደግሞ በቁጥጥር ስር ውለዋል።
የሽብር ቡድኑ ሲጠቀምባቸው የነበሩ የጦር መሳሪዎች መማረካቸውን ጠቁመው፥ በአሁኑ ወቅት ልዩ ወረዳው በተቀናጀ የፀጥታ አስከባሪ ኃይል ቁጥጥር ስር በመዋል የአካባበው ሠላም መመለስ መቻሉን አስታውቀዋል።
በሽብር ቡድኑ የደረሰውን ጠቅላላ ጉዳት በመለየት መልሶ ለማቋቋም የክልሉ መንግሥት እንቅስቀሴ መጀመሩን ምክትል ኃላፊው ገልጸው፥ የልዩ ወረዳው አስተዳደራዊ መዋቅር መልሶ ተደራጅቶ ስራ እስኪጀምር ድረስ ልዩ ወረዳው በተቀናጀ የፀጥታ አስከባሪ ኃይሉ እንዲመራ የክልሉ መንግሥት መወሰኑን አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!