Fana: At a Speed of Life!

በምሥራቅ ኢትዮጵያ በኩል ወደ ውጭ ከተላኩ የግብርና ምርቶች ከ215 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በምሥራቅ የኢትዮጵያ ክፍል በኩል ባለፉት ስድስት ወራት ወደ ውጭ ከተላኩ የግብርና ምርቶች ከ215 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን በንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የድሬዳዋ ወጪ ንግድ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ሐድጎ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ ገቢው የተገኘው ከቡና፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ጫት፣ ጥራጥሬ፣ ቁም እንስሳትና ከሌሎች የግብርና ምርቶች ነው፡፡
ገቢው በግማሽ የበጀት ዓመቱ ለማግኘት ከታቀደው 95 ነጥብ 5 በመቶ ሲሆን፥ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ3 ነጥብ 8 በመቶ ብልጫ አለው ብለዋል፡፡
ምርቶቹ የተላኩት ወደ ምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ፣ ጀርመን፣ ጃፓንና አሜሪካ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
እቅዱን ማሳካት ያልተቻለው ከጥቅምት ወር ጀምሮ የነበረው ደረቃማ የአየር ንብረት በግብርና ምርቶች ላይ ተፅዕኖ በማሳደሩ መሆኑነ ነው አቶ ተስፋዬ የተናገሩት፡፡
በቁም እንስሳት ላይ የሚስተዋለው የኮትሮባንድ ንግድ አለመቆሙ ከዘርፉ ይገኝ የነበረው የውጭ ምንዛሬ ገቢ እንዲቀንስ ማድረጉንም አስረድተዋል፡፡
በቀጣይ በኮትሮባንድ ንግድ ላይ የጠበቀ ቁጥጥር በማድረግና የቁጥጥር ጣቢያዎችን በሰው ኃይልና በቁሳቁስ በማጠናከር ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ የተቀናጀ ሥራን ይጠይቃል ነው ያሉት፡፡
ከድሬዳዋ የንግድ ማህበራት መካከል የቢፍቱ አዱኛ አክሲዮን ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ያሲን መሐመድ፥ በግማሽ የበጀት ዓመቱ ወደ ውጭ ከላኩት የጫት ምርት የ5 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል፡፡
ማህበሩ 10 ሺህ አርሶ አደሮች የአትክልትና ፍራፍሬ በጥራት እንዲያመርቱና በሚመረተው ምርት ላይ እሴት በመጨመር ወደ ውጭ በመላክ የተሻለ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት እየተዘጋጀ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.