Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከአውሮፓ ህብረት አመራሮች ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድርጋቸው ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ቻርልስ ሚሼል እና ከሕብረቱ ዓለም አቀፍ አጋርነት ኮሚሽነር ዩታ ኧርፒላይነን ጋር በብራስልስ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚንስቴር ገለጸ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በ6ኛው የአፍሪካ ኅብረትና የአውሮፓ ኅብረት የጋራ ጉባኤ ለመሳተፍ ቤልጂየም ብራስልስ መግባታቸው ይታወቃል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ቻርልስ ሚሼል እና ከሕብረቱ ዓለም አቀፍ አጋርነት ኮሚሽነር ዩታ ኧርፒላይነን ጋር የኢትዮጵያና የህብረት ወዳጅነት በሚጠናከርበት ጉዳይ ላይ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሣ በስፍራው ለሚገኘው የኢዜአ ሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውይይታቸው ወቅት በኢትዮጵያ ያለውን አሁናዊ ሁኔታ በተመለከተ ለህብረቱ አመራሮች ገለጻ ማድረጋቸውንም ነው ያነሱት።
በኢትዮጵያ ጉዳይ የአውሮፓ ህብረት አባል አገራት መሬት ላይ ያለውን እውነታ እንዲገነዘቡ ለማድረግ በመንግስት በኩል የተለየዩ ጥረቶች እንደተደረጉ ማስታወሳቸውንም ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠቁመዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በኢትዮጵያ ሰላም ለማስፈን በመንግስት የተደረጉ ጥረቶችን አስመልክቶ ማብራሪያ መስጠታቸውንም ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸዋል፡፡
መንግስት በርከት ያሉ የሰላም ጥረቶችን ሲያደርግ ቢቆይም አሸባሪው ህወሓት ግን አሁንም በአፋር ክልል ተደጋጋሚ ጥቃቶችን እየፈጸመ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማንሳታቸውንም ገልጸዋል፡፡
በዚህም ንጹሃን ዜጎችን ለሞት እየዳረገ፣ ብዙዎችን ደግሞ ከቤት ንብረታቸው እያፈናቀለ መሆኑን ጭምር እንደገለጹላቸውም እና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የአሸባሪውን ቡድን ጥፋት ተገንዝቦ ሊያወግዘው እንደሚገባ መናገራቸውንም ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኢትዮጵያ የተከሰተው የድርቅ አደጋ በህብረተሰቡ ላይ ትልቅ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን በውይይቱ ላይ ማንሳታቸው ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ አፋጣኝ ድጋፍ የሚፈልጉ ዜጎች በርካታ መሆናቸውን በመግለጽ መንግስት ከሚያደርገው ድጋፍ ባለፈ የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ መጠየቃቸውንም ነው የገለጹት፡፡
የህብረቱ አመራሮችም የኢትዮጵያ መንግስት በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የጀመረውን ጥረት አድንቀው፥ ጥረቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
መንግስት በአገሪቱ ተጥሎ የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማንሳቱንም የህብረቱ አመራሮች ስለማድነቃቸው ሚኒስትር ድኤታዋ አውስተዋል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.