የጅቡቲ ኩባንያ በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እንዳለው ገለፀ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)”ኢንፔክስ ሶሉሽንስ ፍሪ ዞን” የተሰኘ የጅቡቲ ኩባንያ በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እንዳለው ገለፀ፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን እና የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና አመራሮች ከ”ኢንፔክስ ሶሉሽንስ” የስራ ሀላፊዎች ጋር በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ውይይት አድርገዋል፡፡
በውይይታቸውም በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ያሉ አገልግሎቶች፣ የተቋቋሙበት አላማና ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በተመለከተ በኮርፖሬሽኑ በኩል ለኩባንያው ገለፃ ተደርጓል፡፡
“የኢንፔክስ ሶሉሽንስ ኩባንያ” የስራ እንቅስቃሴዎቹን፣ በዘርፉ ያካበታቸውን ልምዶች እንዲሁም በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ኩባንያው ለማከናወን ስላሰበው ኢንቨስትመንት ዝርዝር ማብራሪያ አቅርቧል፡፡
በቀጣይም “ኢንፔክስ ሶሉሽንስ ኩባንያፍሪ ዞን” በነፃ ንግድ ቀጠናው ኢንቨስትመንቱን ለመጀመር የሚያስችለውን የፕሮጀክት ጥናት ለኮርፖሬሽኑ በማቅረብ ምላሽ ይሰጣል ተብሏል፡፡
ሁለቱ አካላት በቀረቡ ፅሁፎችና መወያያ ነጥቦች ላይ ሰፊ ውይይት ካደረጉ በኋላ በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ያሉ መሰረተ ልማቶችና አገልግሎቶችን መጎብኘታቸውን ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡