የደም ማነስ መንስኤ፣ ምልክቶች እና መፍትሔው
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የደም ማነስ (Anemia) የሚከሰተው ቀይ የደም ሴሎች በበቂ መጠን ሳይኖሩ ሲቀር ነው::
የደም ማነስ የሚባለውም የሂሞግሎቢን መጠን ለወንዶች ከ13 ነጥብ 5 ግራም/ደሊ በታች፣ ለሴቶች ደግሞ ከ12 ግራም/ደሊ በታች ሆኖ ሲገኝ መሆኑ ይገለፃል፡፡
የደም ማነስ መንስዔዎች ወይም አጋላጭ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
ብዙ ሰዎች በተመጣጠነ ምግብ እጥረት፣ በአንጀት መታወክ፣ ሥር በሰደዱ በሽታዎች፣ በኢንፌክሽን እና በሌሎች ሁኔታዎች ምክንያት ለደም ማነስ የተጋለጡ ይሆናሉ።
በወር አበባ ላይ ያሉ ሴቶች፣ ነፍሰጡሮች እና ሥር የሰደደ የጤና እክል ያለባቸው ሰዎች ለዚህ በሽታ በጣም የተጋለጡ መሆናቸውን ከአዲስ አበባ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የደም ማነስ ምልክቶች ምንድን ናቸው?
ከደም ማነስ ምልክቶች ውስጥ የድካም ስሜት፣ ራስ ምታት፣ የትንፋሽ ማጠር፣ የቆዳ መገርጣት እና መድረቅ፣ የልብ ምት መጨመር፣ በታችኛው እግር ላይ ያልታሰበ እንቅስቃሴ፣ ቀዝቃዛ እጅ እና እግር፣ በአንዱ ወይም በሁለቱም ጆሮዎች ላይ ያልተለመደ ድምጽ ወይም ጩኸት ይጠቀሳል፡፡
የደም ማነስ ችግር መፍትሔው:¬-
የደም ማነስ ካለብዎት የአይረን መጠናቸው ከፍተኛ የሆኑ ምግቦችን እንደ የበሬ ሥጋ፣ አረንጓዴ ቅጠላማ አትክልቶች፣ ለውዝ፣ የወተት ተዋጽኦዎች፣ የፎሊክ አሲድ ይዘታቸው ከፍተኛ የሆኑ ምግቦች እንደ ሎሚ እና ብርቱካን፣ እና ጥራጥሬዎች መመገብ ይመከራል::