Fana: At a Speed of Life!

ህጻናት ላይ የሚከሰተው የዐይን ካንሰር ምልክቶች እና ህክምናው

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓይን ካንሰር (ረቲኖብላስቶማ) በዓይን የኋላኛው ክፍል ብርሃን መቀበያ ረቲና የሚነሳ የካንሰር ዓይነት ነው፡፡

የህጻናት የዓይን ካንሰር ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር አዲሱ ወርቁ ህጻናት ላይ ስለሚከሰተው የዓይን ካንሰር ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

በቆይታቸው እንደገለጹት ፥ የዓይን ካንስር አልፎ አልፎ በዘር ሊተላለፍ እንደሚችል የሚገለጽ ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ መነሻ ምክንያቱ አይታወቅም፡፡

ይህም የኋላኛው የዓይን ክፍል እድገትን በማዛባት ጤነኛ ያልሆኑ ህዋሶች ቁጥር እየጨመሩ እንዲመጡና ህዋሶቹ ወደዓይን የውስጥ ክፍል ወይም ከዓይን ኳሱ ውጪ ያድጋሉ፡፡

ይህም በአብዛኛው የሚታወቀው ከ2ዓመት እስከ 5ዓመት በሚሆናቸው ህጻናት ላይ እንደሆነ ዶክተር አዲሱ ገልጸው ፥ ከ6ዓመት በላይ በሆኑ ህጻናት ላይ በአብዛኛው እንደማይታይም ነው የተናገሩት፡፡

ይህ ካንሰር ከሌሎች ካንሰር የሚለየው ገና ባልጠና ወይም ባላደገ ረቲና(የዓይን የኋላናው ግድግዳ) ላይ ያሉ ሴሎችን ማጥቃቱ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በዚህም የዓይን ካንሰር የሚመጣውም የሚታየውም በልጅነት ጊዜ እንደሆነ የተናገሩ ሲሆን ፥ ሲወለዱ ጀምሮ ሊኖር እንደሚችልና በጊዜ ሂደት እያደገ የሚመጣ የካንሰር ዓይነት እንደሆነም ነው የተናገሩት፡፡

የዓይን ካንሰር ሁለት ዋና ዋና ምልክቶች አሉት፡-

የዓይን ብሌን ወይም ጥቁሩ ክፍል ነጭ ሲሆንና
የዓይን መንሸዋረር (ወደውስጥም ወደውጭም) ናቸው፡፡
በእነዚህ ሁለት ምልክቶች የዓይን ካንሰር መኖር አለመኖሩን ማወቅ እንደሚቻልም ገልጸዋል፡፡

በዓለም ላይ ከሚወለዱ ከ15ሺህ እስከ 20 ሺኅ ከሚሆኑ ህጻናት 1 ሰው ላይ እንደሚከሰትም ጥናቶች እንሚያሳዩ የዘርፉ ባለሙያው ዶክተር አዲሱ ተናግረዋል፡፡

በዚህም በኢትዮጵያ እስከ 300 የሚሆኑ ህጻናት በካንሰር ተይዘው በየዓመቱ ይወለዳሉም ነው ያሉት፡፡

ይህን ተከትሎም ህጻናት ላይ የሚከሰተውን የዓይን ካንሰር በጊዜ ካልተገኘና ህክምና ካላደረጉ ለህልፈት እንደሚዳረጉና ማስተዋል እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የሚወሰደው እርምጃና የሕክምና ሂደቱ
• በመጀመሪያ ህይዎት ማትረፍ፣
• የዓይን ኳሱን ማትረፍ እና
• እይታን ማትረፍ እንደሆነም ነው የተነሳው፡፡

ካንሰሩ በጊዜ ከተደረሰበት ከኋላኛው የዓይን ግድግዳ ላይ ካንሰሩ እንዳለ በሌዘርና ሌሎች መንገዶች ህክምና ማዳን እንደሚቻልም ነው የተናገሩት፡፡

ሆኖም በጊዜ ካልተደረሰበት የካንሰሩ ዓይነት በፍጥነት የሚያድግ በመሆኑ የዓይን ኳስ ላይ ብቻ ከሆነ ኳሱን በማውጣት ህይዎትን ለማትረፍ ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ከዓይን ኳስ ውጪ ካንሰሩ ከሰፋ የኬሞቴራፒ ህክምና በማድረግ ህይዎትን ለማትረፍ ጥረት እንደሚደረግም ነው የጠቆሙት፡፡

በዚህም ዓይን ላይ የሚታዩ መሰል ምልክቶችን በማስተዋል ህጻናት በፍጥነት ህክምና እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የህጻናት የዓይን ካንሰር ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር አዲሱ ወርቁ መክረዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.