ዶ/ር ሊያ ታደሰ ከሩሲያ ልዑክ ጋር የጤና ስርዓትን በማጠናከር ዙርያ መከሩ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ከሩሲያ መንግስት የልዑካን ቡድን አባላት ጋር የጤና ስርዓትን በማጠናከር ዙርያ የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል፡፡
በውይይቱም በሀገራቱ መካከል ያለውን ዘርፈ ብዙ ትብብር በማንሳት ከ100 ዓመታት በላይ አገልግሎት የሰጠው የባልቻ አጠቃላይ ሆስፒታል እየሰጠ ያለውን አገልግሎትና ጥራቱን ለማሻሻል መሰራት በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
ሆስፒታሉ ለረጅም ዓመታት አገልግሎት በመስጠቱ አሁን ላይ የመሰረተ ልማት ማሻሻያ ለማድረግና በተለያዩ ዘመናዊ የሕክምና ግብዓቶች ማደራጀት እንደሚያስፈልግም ነው የተገለጸው፡፡
ለዚህም የሩሲያ መንግስትና የሀገሪቱ ቀይመስቀል ኮሚቴ ኃላፊነቱን ወስዶ ወደ ስራ እየገባ መሆኑ በውይይቱ ወቅት ተነስቷል።
እንዲሁም የባለሙያዎችን እውቀትና ክህሎት በአጭርና በረጅም ጊዜ ስልጠና ከማጎልበት አኳያ በተለይም በእናቶችና ሕጻናት ጤና እንዲሁም ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በመከላከልና በመቆጣጠር ዙርያም ውይይት ተካሂዷል፡፡
ዶ/ር ሊያ ታደሰ በዚሁ ወቅት÷ በኢትዮጵያ የተዘረጉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን እና የተመቻቹ ሁኔታዎችን ለቡድኑ አብራርተዋል፡፡
የሩሲያ ተቋማት በኢትዮጵያ በፋርማሲቲካል ዘርፍ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱም መጠየቃቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡